መዝሙር 69:22-36

መዝሙር 69:22-36 NASV

በፊታቸው ያለው ማእድ ወጥመድ ይሁንባቸው፤ ለማኅበራቸውም እንቅፋት ይሁን። ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፤ ወገባቸውም ለዘላለም ይጕበጥ። መዓትህን በላያቸው አፍስስ፤ የቍጣህም መቅሠፍት ድንገት ይድረስባቸው። ሰፈራቸው ባድማ ይሁን፤ በድንኳኖቻቸው የሚኖር አይገኝ፤ አንተ የመታሃቸውን አሳድደዋልና፤ ያቈሰልሃቸውንም ሥቃያቸውን አባብሰዋል። በበደላቸው በደል ጨምርባቸው፤ ወደ ጽድቅህም አይግቡ። ከሕይወት መጽሐፍ ይደምሰሱ፤ ከጻድቃንም ጋራ አይጻፉ። ነገር ግን እኔ በሥቃይና በጭንቅ ላይ እገኛለሁ፤ አምላክ ሆይ፤ ማዳንህ ደግፎ ይያዘኝ። የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አወድሳለሁ፤ በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። ከበሬ ይልቅ፣ ቀንድና ጥፍር ካበቀለ እንቦሳ ይልቅ ይህ እግዚአብሔርን ደስ ያሠኘዋል። ድኾች ይህን ያያሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤ እናንተ እግዚአብሔርን የምትሹ ልባችሁ ይለምልም! እግዚአብሔር ድኾችን ይሰማልና፤ በእስራት ያለውንም ሕዝቡን አይንቅም። ሰማይና ምድር፣ ባሕርም፣ በውስጣቸውም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመስግኑት። እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና፤ የይሁዳንም ከተሞች መልሶ ይሠራቸዋልና፤ ሕዝቡም በዚያ ይሰፍራል፤ ይወርሳታልም። የባሪያዎቹም ዘሮች ይወርሷታል፤ ስሙንም የሚወድዱ በዚያ ይኖራሉ።