የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 68:1-18

መዝሙር 68:1-18 NASV

እግዚአብሔር ይነሣ፤ ጠላቶቹ ይበተኑ፤ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ። ጢስ እንደሚበንን፣ እንዲሁ አብንናቸው። ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፣ ክፉዎችም እንዲሁ ከእግዚአብሔር ፊት ይጥፉ። ጻድቃን ግን ደስ ይበላቸው፤ በእግዚአብሔር ፊት ሐሤት ያድርጉ፤ ደስታንና ፍሥሓን የተሞሉ ይሁኑ። ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ለስሙም ተቀኙ፤ በደመናት ላይ የሚሄደውን ከፍ አድርጉት፤ ስሙ እግዚአብሔር በተባለው ፊት፣ እጅግ ደስ ይበላችሁ። እግዚአብሔር በተቀደሰ ማደሪያው፣ ለድኻ አደጉ አባት፣ ለባልቴቲቱም ተሟጋች ነው። እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤተ ሰብ መካከል ያኖራል፤ እስረኞችን ነጻ አውጥቶ ያስፈነድቃል፤ ዐመፀኞች ግን ምድረ በዳ ይኖራሉ። እግዚአብሔር ሆይ፤ በሕዝብህ ፊት በወጣህ ጊዜ፣ በምድረ በዳም በተጓዝህ ጊዜ፣ ሴላ በሲና አምላክ፣ በእግዚአብሔር ፊት፣ በእስራኤል አምላክ፣ በእግዚአብሔር ፊት፣ ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ሰማያትም ዶፍ አወረዱ። እግዚአብሔር ሆይ፣ በቂ ዝናብ አዘነብህ፤ ክው ብሎ የደረቀውን ርስትህን አረሰረስህ። መንጋህ መኖሪያው አደረጋት፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከበረከትህ ለድኾች ሰጠህ። ጌታ እንዲህ ሲል ቃሉን አስተላለፈ፤ ትእዛዙን የሚያውጁትም ብዙ ሰራዊት ናቸው፤ “የሰራዊት ነገሥታት ፈጥነው ይሸሻሉ፤ በሰፈር የዋሉ ሴቶችም ምርኮን ተካፈሉ። በበጎች በረት መካከል ብትገኙ እንኳ፣ ከብር እንደ ተሠሩ የርግብ ክንፎች፣ በቅጠልያ ወርቅ እንደ ተለበጡ ላባዎች ናችሁ።” ሁሉን ቻዩ በዚያ የነበሩትን ነገሥታት በበተነ ጊዜ፣ በሰልሞን እንደሚወርድ በረዶ አደረጋቸው። አንተ ብርቱ ተራራ፣ የባሳን ተራራ ሆይ፤ አንተ ባለብዙ ጫፍ ተራራ፣ የባሳን ተራራ፤ እናንተ ባለብዙ ጫፍ ተራሮች ሆይ፤ እግዚአብሔር ሊኖርበት የመረጠውን ተራራ፣ በርግጥ እግዚአብሔር ለዘላለም የሚኖርበትን ተራራ ለምን በቅናት ዐይን ታያላችሁ? የእግዚአብሔር ሠረገላዎች እልፍ አእላፍ ናቸው፤ ሺሕ ጊዜም ሺሕ ናቸው፤ ጌታ ከሲና ወደ መቅደሱ ገባ። ወደ ላይ ዐረግህ፤ ምርኮ አጋበስህ፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ አንተ በዚያ ትኖር ዘንድ፣ ከዐመፀኞችም ሳይቀር፣ ከሰዎች ስጦታን ተቀበልህ።