መዝሙር 60
60
መዝሙር 60
ከሽንፈት በኋላ የቀረበ ብሔራዊ ጸሎት
60፥5-12 ተጓ ምብ – መዝ 108፥6-13
ለመዘምራን አለቃ፤ “የኪዳን ጽጌረዳ” በሚለው ቅኝት የሚዘመር፤#60 ርእሱ የሥነ ጽሑፉን ቅርጽ ወይም የመዝሙሩን ሁኔታ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። በሰሜናዊ ምዕራብ መስጴጦምያና#60 ርእሱ የአራማውያን ወይም የሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ነው። በማእከላዊ ሶርያ የሚኖሩትን አራማውያን#60 ርእሱ በመካከለኛው ሶርያ የሚገኙት አራማውያንን የሚያመለክት ነው። በወጋቸው ጊዜ፣ ኢዮአብም ተመልሶ በጨው ሸለቆ ዐሥራ ሁለት ሺሕ ኤዶማውያንን በፈጀ ጊዜ፣ ለትምህርት፤ የዳዊት ቅኔ።
1እግዚአብሔር ሆይ፤ ጣልኸን፤ አንኰታኰትኸን፤
ተቈጣኸንም፤ አሁን ግን መልሰህ አብጀን።
2ምድሪቱን አናወጥሃት፤ ፍርክስክስ አደረግሃት፤
ትንገዳገዳለችና ስብራቷን ጠግን።
3ለሕዝብህ አበሳውን አሳየኸው፤
ናላ የሚያዞር የወይን ጠጅ እንድንጠጣም ሰጠኸን።
4ነገር ግን ከቀስት እንዲያመልጡ፣
ለሚፈሩህ ምልክት አቆምህላቸው። ሴላ
5ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ፣
በቀኝ እጅህ ርዳን፤ መልስም ስጠን።
6እግዚአብሔር ከመቅደሱ እንዲህ ሲል ተናገረ፤
“ደስ እያለኝ የሴኬምን ምድር እሸነሽናለሁ፤
የሱኮትን ሸለቆ አከፋፍላለሁ።
7ገለዓድ የእኔ ነው፤ ምናሴም የእኔ ነው፤
ኤፍሬም የራስ ቍሬ ነው፤
ይሁዳም በትረ መንግሥቴ ነው።
8ሞዓብ የመታጠቢያ ገንዳዬ ነው፤
በኤዶምያስ ላይ ጫማዬን እወረውራለሁ፤
በፍልስጥኤም ላይ በድል እልል እላለሁ።”
9ወደ ተመሸገው ከተማ ማን ያመጣኛል?
ማንስ ወደ ኤዶምያስ ይመራኛል?
10አምላክ ሆይ፤ የጣልኸን አንተ አይደለህምን?
እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰራዊታችን ጋር እኮ አልወጣ አልህ!
11በጠላት ላይ ድልን አቀዳጀን፤
የሰው ርዳታ ከንቱ ነውና።
12በእግዚአብሔር ክንደ ብርቱ እንሆናለን፤
ጠላቶቻችንን የሚረጋግጥልን እርሱ ነውና።
Currently Selected:
መዝሙር 60: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.