መዝሙር 59
59
መዝሙር 59
ክፉዎችን በመቃወም የቀረበ ጸሎት
ለመዘምራን አለቃ፤ “አታጥፋ” በሚለው ቅኝት የሚዜም፤ ዳዊትን ለመግደል ሰዎች ቤቱን ከብበው እንዲጠብቁት ሳኦል በላካቸው ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ#59 ርእሱ የሥነ ጽሑፉን ቅርጽ ወይም የመዝሙሩን ሁኔታ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።።
1አምላክ ሆይ፤ ከጠላቶቼ እጅ አድነኝ፤
ሊያጠቁኝ ከሚነሡብኝም ጠብቀኝ።
2ከክፉ አድራጊዎች ታደገኝ፤
ደም ከተጠሙ ሰዎችም አድነኝ።
3እነሆ በነፍሴ ላይ አድብተዋልና፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ ጨካኞች ያለ በደሌ፣ ያለ ኀጢአቴ
በላዬ ተሰብስበው ዶለቱብኝ።
4እነርሱ ያለ በደሌ ሊያጠቁኝ ተዘጋጅተው መጡ፤
አንተ ግን ትረዳኝ ዘንድ ተነሥ፤ ሁኔታዬንም ተመልከት።
5የሰራዊት አምላክ የሆንህ፣ አንተ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤
ሕዝቦችን ሁሉ ለመቅጣት ተነሥ፤
በተንኰላቸው በደል የሚፈጽሙትንም ሁሉ አትማራቸው። ሴላ
6እንደ ውሻ እያላዘኑ፣
በምሽት ተመልሰው ይመጣሉ፤
በከተማዪቱም ዙሪያ ይራወጣሉ።
7ከአፋቸው የሚወጣውን ተመልከት፤
ሰይፍ በከንፈራቸው ላይ አለ፤
“ማን ሊሰማን ይችላል?” ይላሉና።
8 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ትሥቅባቸዋለህ፤
ሕዝቦችን ሁሉ በንቀት ታያቸዋለህ።
9ብርታቴ ሆይ፤ አንተን እጠብቃለሁ፤
አምላክ ሆይ፤ አንተ መጠጊያዬ ነህና።
10እግዚአብሔር በምሕረቱ ይገናኘኛል፤
አምላኬ የጠላቶቼን ውድቀት ያሳየኛል።
11ጋሻችን#59፥11 ወይም ልዑል ተብሎ መተርጐም ይችላል። ጌታ ሆይ፤ አትግደላቸው፤
አለዚያ ሕዝቤ ይረሳል፤
በኀይልህ አንከራትታቸው፤
ዝቅ ዝቅም አድርጋቸው።
12ከአፋቸው ስለሚወጣው ኀጢአት፣
ከከንፈራቸውም ስለሚሰነዘረው ቃል፣
በትዕቢታቸው ይያዙ።
ስለ ተናገሩት መርገምና ውሸት፣
13በቍጣ አጥፋቸው፤
ፈጽመህም አስወግዳቸው፤
በዚህም እግዚአብሔር የያዕቆብ ገዥ መሆኑ፣
እስከ ምድር ዳርቻ ይታወቃል። ሴላ
14እንደ ውሻ እያላዘኑ፣
በምሽት ተመልሰው ይመጣሉ፤
በከተማዪቱም ዙሪያ ይራወጣሉ።
15ምግብ ፍለጋ ይራወጣሉ።
ካልጠገቡም ያላዝናሉ።
16እኔ ግን ስለ ኀይልህ እዘምራለሁ፤
በማለዳም ስለ ምሕረትህ እዘምራለሁ፤
አንተ መጠጊያዬ፣
በመከራም ቀን ዐምባዬ ነህና።
17ብርታቴ ሆይ፤ ውዳሴ አቀርብልሃለሁ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መጠጊያዬ፣
የምትወድደኝም አምላኬ ነህና።
Currently Selected:
መዝሙር 59: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.