ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ። ቀን ለሌላው ቀን ይናገራል፤ ሌሊትም ለሌሊት ዕውቀትን ይገልጣል፤ ንግግር የለም፤ ቃል የለም፤ ድምፃቸው በጆሮ የሚሰማ አይደለም። ያም ሆኖ ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፣ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ይወጣል። እርሱ በሰማያት ለፀሓይ ድንኳን ተክሏል፤ ፀሓይም ከእልፍኙ እንደሚወጣ ሙሽራ ይወጣል፤ ወደ ግቡም እንደሚሮጥ ብርቱ ሰው ደስ ይለዋል። መውጫው ከሰማያት ዳርቻ ነው፤ ዑደቱም እስከ ሌላኛው ዳርቻ ነው፤ ከትኵሳቱም የሚሰወር የለም። የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስንም መልሶ ያለመልማል፤ የእግዚአብሔር ሥርዐት የታመነ ነው፤ አላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል። የእግዚአብሔር ሕግጋት ትክክል ናቸው፤ ልብን ደስ ያሰኛሉ። የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፤ ዐይንን ያበራል። እግዚአብሔርን መፍራት ንጹሕ ነው፤ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። የእግዚአብሔር ፍርድ የታመነ፣ ሁለንተናውም ጻድቅ ነው፤ ከወርቅ ይልቅ የከበረ፣ እጅግ ከጠራ ወርቅም የተሻለ ነው፤ ከማር ይልቅ ይጣፍጣል፤ ከማር ወለላም ይበልጥ ይጥማል። ደግሞም አገልጋይህ በእርሱ ጥንቃቄ ያደርጋል፤ እርሱንም መጠበቅ ወሮታ አለው። ስሕተቱን ማን ሊያስተውል ይችላል? ከተሰወረ በደል አንጻኝ። ባሪያህን ከድፍረት ኀጢአት ጠብቅ፤ እንዳይሠለጥንብኝም ርዳኝ፤ ያን ጊዜ ያለ እንከን እሆናለሁ፤ ከታላቅ በደልም እነጻለሁ። መጠጊያዬና አዳኜ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአፌ ቃልና የልቤ ሐሳብ፣ በፊትህ ያማረ ይሁን።
መዝሙር 19 ያንብቡ
ያዳምጡ መዝሙር 19
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መዝሙር 19:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos