የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 18:25-50

መዝሙር 18:25-50 NASV

ለታማኝ ሰው ታማኝ መሆንህን፣ ለፍጹም ሰው ፍጹም መሆንህን ታሳያለህ። ለንጹሕ ሰው አንተም ንጹሕ መሆንህን፣ ለጠማማ ሰው ግን አንተም ጠማማ መሆንህን ታሳያለህ። አንተ ትሑታንን ታድናለህ፤ ትዕቢተኛውን ዐይን ግን ታዋርዳለህ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መብራቴን ታበራለህ፤ አምላኬ፤ ጨለማዬን ያበራል። በአንተ ጕልበት በሰራዊት ላይ እረማመዳለሁ፤ በአምላኬም ኀይል ቅጥር እዘላለሁ። የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔርም ቃል የነጠረ ነው። መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ፣ ጋሻ ነው። ከእግዚአብሔር በቀር ማን አምላክ አለ? ከአምላካችንስ በቀር ዐለት ማን ነው? ኀይልን የሚያስታጥቀኝ፣ መንገዴንም የሚያቀና እርሱ እግዚአብሔር ነው። እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ አጽንቶ ያቆመኛል። እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናቸዋል፤ ክንዶቼም የናስ ቀስት መገተር ይችላሉ። የማዳንህን ጋሻ ሰጥተኸኛል፤ ቀኝ እጅህም ደግፋ ይዛኛለች፤ ድጋፍህ ታላቅ አድርጎኛል። ከሥሬ ያለውን ስፍራ ለአረማመዴ አሰፋህልኝ፤ እግሬም አልተንሸራተተም። ጠላቶቼን አሳድጄ ያዝኋቸው፤ እስኪጠፉም ድረስ ወደ ኋላ አልተመለስሁም። እንዳያንሰራሩ አድርጌ አደቀቅኋቸው፤ ከእግሬም ሥር ወደቁ። አንተ ለጦርነት ኀይልን አስታጠቅኸኝ፤ ባላንጦቼ እግሬ ላይ እንዲደፉ አደረግህ። ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው እንዲሸሹ አደረግህ፤ እኔም የሚጠሉኝን አጠፋኋቸው። ለርዳታ ጮኹ፤ የሚያስጥላቸው ግን አልነበረም፤ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱ ግን አልመለሰላቸውም። ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ አደቀቅኋቸው፤ እንደ መንገድ ላይ ጭቃም ረገጥኋቸው። በሕዝብ ከተቃጣብኝ አደጋ አዳንኸኝ፤ የሕዝቦች መሪ አድርገህ አስቀመጥኸኝ፤ የማላውቀውም ሕዝብ ተገዛልኝ። የባዕድ አገር ሰዎች ይፈሩኛል፤ እንደ ሰሙኝም ወዲያውኑ ይታዘዙኛል። ባዕዳን ፈሩ፤ ከምሽጋቸውም እየተንቀጠቀጡ ወጡ። እግዚአብሔር ሕያው ነው! ዐለቴ የተባረከ ይሁን! የድነቴ አምላክ ከፍ ከፍ ይበል። እርሱ በቀሌን የሚመልስልኝ፣ አሕዛብንም የሚያስገዛልኝ አምላክ ነው፤ ከጠላቶቼም የሚታደገኝ እርሱ ነው። አንተ ከባላንጦቼ በላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ፤ ከጨካኞች አዳንኸኝ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሆይ፤ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ስምህንም በመዝሙር እወድሳለሁ። እርሱ ላነገሠው ታላላቅ ድሎችን ይሰጣል፤ ጽኑ ፍቅሩንም ለቀባው፣ ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይገልጣል።