ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው። የጽድቅ ሕግህን ለመጠበቅ፤ ምያለሁ፤ ይህንኑ አጸናለሁ። እጅግ ተቸግሬአለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ በከንፈሬ ያቀረብሁትን የበጎ ፈቃድ ስጦታ ተቀበል፤ ሕግህንም አስተምረኝ። ነፍሴ ዘወትር አደጋ ላይ ናት፤ ሕግህን ግን አልረሳሁም። ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤ እኔ ግን መመሪያህን አልተላለፍሁም። ምስክርነትህ የዘላለም ውርሴ ናት፤ ልቤ በዚህ ሐሤት ያደርጋልና። ትእዛዝህን ለዘላለም፣ እስከ ወዲያኛው ለመፈጸም፣ ልቤን ወደዚያው አዘነበልሁ። መንታ ልብ ያላቸውን ጠላሁ፤ ሕግህን ግን ወደድሁ። አንተ መጠጊያዬና ጋሻዬ ነህ፤ ቃልህን በተስፋ እጠብቃለሁ። የአምላኬን ትእዛዞች እጠብቅ ዘንድ፣ እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ራቁ። እንደ ቃልህ ደግፈኝ፤ እኔም ሕያው እሆናለሁ፤ ተስፋዬም መና ቀርቶ አልፈር። ያለ ሥጋት እቀመጥ ዘንድ ደግፈህ ያዘኝ፤ ሥርዐትህንም ዘወትር እመለከታለሁ። መሠሪነታቸው በከንቱ ነውና፣ ከሥርዐትህ ውጭ የሚሄዱትን ሁሉ ወዲያ አስወገድሃቸው። የምድርን ክፉዎች ሁሉ እንደ ጥራጊ አስወገድሃቸው፤ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ። ሥጋዬ አንተን በመፍራት ይንቀጠቀጣል፤ ፍርድህንም እፈራለሁ። ፍትሕና ጽድቅ ያለበትን ሠርቻለሁ፤ ለሚጨቍኑኝ አሳልፈህ አትስጠኝ። ለባሪያህ በጎነት ዋስትና ሁን፤ እብሪተኞች እንዲጨቍኑኝ አትፍቀድላቸው። ዐይኖቼ ማዳንህን፣ የጽድቅ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ። ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ መጠን አድርግ፤ ሥርዐትህንም አስተምረኝ። እኔ ባሪያህ ነኝ፤ ምስክርነትህን ዐውቅ ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕግህ እየተጣሰ ነውና፣ ጊዜው አንተ የምትሠራበት ነው። ስለዚህ ከወርቅ፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ፣ ትእዛዞችህን ወደድሁ። መመሪያህ ሙሉ በሙሉ ልክ ነው አልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ። ምስክርነትህ ሁሉ ድንቅ ነው፤ ስለዚህ ነፍሴ ትጠብቀዋለች። የቃልህ ትርጓሜ ያበራል፤ አላዋቂዎችንም አስተዋዮች ያደርጋል። ትእዛዝህን ናፍቄአለሁና፣ አፌን ከፈትሁ፤ አለከለክሁም። ስምህን ለሚወድዱ ማድረግ ልማድህ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ወደ እኔ ተመልሰህ ምሕረት አድርግልኝ። አካሄዴን እንደ ቃልህ ቀና አድርግልኝ፤ ኀጢአትም በላዬ እንዲሠለጥን አትፍቀድ። ትእዛዝህን መጠበቅ እንድችል፣ ከሰዎች ጥቃት ታደገኝ። በባሪያህ ላይ ፊትህን አብራ፤ ሥርዐትህንም አስተምረኝ። ሕግህ ባለመከበሩ፤ እንባዬ እንደ ውሃ ይፈስሳል። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ፍርድህም ትክክል ነው። ምስክርነትህን በጽድቅ አዘዝህ፤ እጅግ አስተማማኝም ነው። ጠላቶቼ ቃልህን ዘንግተዋልና፣ ቅናት አሳረረኝ። ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፤ ባሪያህም ወደደው። እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፤ ነገር ግን መመሪያህን አልዘነጋሁም። ጽድቅህ ዘላለማዊ ጽድቅ ነው፤ ሕግህም እውነት ነው። መከራና ሥቃይ ደርሶብኛል፤ ነገር ግን ትእዛዝህ ደስታዬ ነው። ምስክርነትህ ለዘላለም የጽድቅ ምስክርነት ነው፤ በሕይወት እኖር ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ።
መዝሙር 119 ያንብቡ
ያዳምጡ መዝሙር 119
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መዝሙር 119:105-144
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች