የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 119:1-24

መዝሙር 119:1-24 NASV

ብፁዓን ናቸው፤ መንገዳቸው ነቀፋ የሌለበት፣ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ፤ ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔር ሕግ፤ ምስክርነቱን የሚጠብቁ፣ በፍጹምም ልብ የሚሹት፤ ዐመፅን አያደርጉም፤ ነገር ግን በመንገዱ ይሄዳሉ። ጠንቅቀን እንጠብቃት ዘንድ፣ አንተ ሥርዐትን አዝዘሃል። ሥርዐትህን እጠብቅ ዘንድ፣ ምነው መንገዴ ጽኑ በሆነልኝ ኖሮ! ወደ ትእዛዞችህ ስመለከት፣ በዚያ ጊዜ አላፍርም። የጽድቅ ፍርድህን ስማር፣ በቅን ልብ ምስጋና አቀርብልሃለሁ። ሥርዐትህን እጠብቃለሁ፤ ፈጽመህ አትተወኝ። ጕልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል? በቃልህ መሠረት በመኖር ነው። በሙሉ ልቤ ፈለግሁህ፤ ከትእዛዞችህ ፈቀቅ እንዳልል አድርገኝ። አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። ከአንደበትህ የሚወጣውን ደንብ ሁሉ፣ በከንፈሬ እናገራለሁ። ሰው በሀብቱ ብዛት ደስ እንደሚለው፣ ምስክርነትህን በመከተል ደስ ይለኛል። ድንጋጌህን አሰላስላለሁ፤ ልቤን በመንገድህ ላይ ጥያለሁ። በሥርዐትህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልዘነጋም። ሕያው እንድሆን፣ ቃልህንም እንድጠብቅ፣ ለአገልጋይህ መልካም አድርግ። ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ ዐይኖቼን ክፈት። እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝ፤ ትእዛዞችህን ከእኔ አትሰውር። ዘወትር ደንብህን በመናፈቅ፣ ነፍሴ እጅግ ዛለች። ከትእዛዞችህ የሳቱትን፣ እብሪተኞችንና ርጉሞችን ትገሥጻለህ። ምስክርነትህን ጠብቄአለሁና፣ ስድብንና ንቀትን ከእኔ አርቅ። ገዦች ተቀምጠው ቢዶልቱብኝ እንኳ፣ አገልጋይህ ሥርዐትህን ያሰላስላል። ምስክርነትህ ለእኔ ደስታዬ ነው፤ መካሪዬም ነው።