መዝሙር 118
118
መዝሙር 118
ለዳስ በዓል የቀረበ የጕዞ መዝሙር
1 እግዚአብሔር ቸር ነውና አመስግኑት፤
ምሕረቱም ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።
2የእስራኤል ሕዝብ፣ “ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበል።
3የአሮን ቤት፣ “ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበል።
4 እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፣
“ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበሉ።
5በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤
እግዚአብሔርም መለሰልኝ፤ ከመጠበብም አወጣኝ።
6 እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?
7ይረዳኝ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው፤
የጠላቶቼንም ውድቀት አያለሁ።
8ሰውን መከታ ከማድረግ ይልቅ፣
በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።
9በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ፣
በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።
10ሕዝቦች ሁሉ ከበቡኝ፤
ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ።
11መክበቡንስ በየአቅጣጫው ከበቡኝ፤
ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ።
12እንደ ንብ መንጋ ከበቡኝ፤
ነገር ግን እንደሚነድድ እሾኽ ከሰሙ፤
በርግጥም በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ።
13ተገፍትሬ ልወድቅ ተንገደገድሁ፤
እግዚአብሔር ግን ረዳኝ።
14 እግዚአብሔር ብርታቴና ዝማሬዬ ነው፤
አዳኝ ሆነልኝ።
15በጻድቃን ድንኳን የእልልታና የሆታ ድምፅ፣
እንዲህ እያለ ያስተጋባል፤
“የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ብርቱ ሥራ ሠራች፤
16 የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ከፍ ከፍ አለች፤
የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ብርቱ ሥራ ሠራች።”
17ተርፌ በሕይወት እኖራለሁ እንጂ አልሞትም፤
የእግዚአብሔርንም ሥራ ገና እናገራለሁ።
18መገሠጹን እግዚአብሔር እጅግ ገሥጾኛል፤
ነገር ግን ለሞት አሳልፎ አልሰጠኝም።
19የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፤
በዚያ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
20ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት፤
ጻድቃን በእርሷ በኩል ይገባሉ።
21ሰምተህ መልሰህልኛልና፣
አዳኝም ሆነህልኛልና አመሰግንሃለሁ።
22ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣
እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።
23 እግዚአብሔር ይህን አደረገ፤
ለዐይናችንም ድንቅ ናት።
24 እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤
በእርሷ ሐሤት እናድርግ፤ ደስም ይበለን።
25 እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ አድነን፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ አሳካልን።
26 በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው።
ከእግዚአብሔር ቤት ባረክናችሁ።
27 እግዚአብሔር አምላክ ነው፤
ብርሃኑንም በላያችን አበራ፤
እስከ መሠዊያው#118፥27 ወይም የክብረ በዓልን መሥዋዕት በገመድ ማሰር ወይም መውሰድ ቀንዶች ድረስ በመውጣት፣
ዝንጣፊ ይዛችሁ በዓሉን ከሚያከብሩት ጋር ተቀላቀሉ።
28አንተ አምላኬ ነህ፤ አመሰግንሃለሁ፤
አንተ አምላኬ ነህ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ።
29ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
ምሕረቱም ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።
Currently Selected:
መዝሙር 118: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.