ሃሌ ሉያ። ቸር ነውና፣ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ስለ እግዚአብሔር ታላቅ ሥራ ማን ሊናገር ይችላል? ምስጋናውንስ ሁሉ ማን ተናግሮ ይጨርሳል? ብፁዓን ናቸው፤ ፍትሕ እንዳይዛነፍ የሚጠብቁ፣ ጽድቅን ሁልጊዜ የሚያደርጉ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለሕዝብህ ሞገስ ስታድል ዐስበኝ፤ በምታድናቸውም ጊዜ ርዳኝ፤ ይኸውም የምርጦችህን ብልጽግና አይ ዘንድ፣ በሕዝብህ ደስታ ደስ ይለኝ ዘንድ፣ ከርስትህም ክብር የተነሣ እጓደድ ዘንድ ነው። እኛም እንደ አባቶቻችን ኀጢአት ሠራን፤ በደልን፤ ክፉም አደረግን። አባቶቻችን በግብጽ ሳሉ፣ ታምራትህን አላስተዋሉም፤ የምሕረትህን ብዛት አላሰቡም፤ በባሕሩ አጠገብ፣ ገና ቀይ ባሕር አጠገብ ዐመፁብህ። እርሱ ግን የኀይሉን ታላቅነት ለማሳወቅ፣ ስለ ስሙ አዳናቸው። ቀይ ባሕርን ገሠጸ፤ እርሱም ደረቀ፤ በምድረ በዳ እንደሚታለፍ በጥልቅ ውሃ መካከል መራቸው። ከባላጋራቸው እጅ አዳናቸው፤ ከጠላትም እጅ ታደጋቸው። ባላንጦቻቸውን ውሃ ዋጣቸው፤ ከእነርሱም አንድ አልተረፈም። ከዚህ በኋላ የተስፋ ቃሉን አመኑ፤ በዝማሬም አመሰገኑት። ነገር ግን ያደረገውን ወዲያውኑ ረሱ፤ በምክሩም ለመሄድ አልታገሡም። በምድረ በዳ እጅግ መመኘት አበዙ፤ በበረሓም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት። እርሱም የለመኑትን ሰጣቸው፤ ዳሩ ግን የሚያኰሰምን ሕመም ሰደደባቸው። በሰፈር በሙሴ ላይ፣ ለእግዚአብሔር በተቀደሰውም በአሮን ላይ ቀኑ። ምድር ተከፍታ ዳታንን ዋጠች፤ የአቤሮንን ወገን ሰለቀጠች። እሳት በጉባኤያቸው መካከል ነደደ፤ ነበልባሉም ክፉዎችን ፈጅቶ አስወገደ። በኮሬብ ጥጃ ሠሩ፤ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ። ክብራቸው የሆነውንም ሣር በሚበላ፣ በበሬ ምስል ለወጡ። በግብጽ ታላቅ ነገር ያደረገውን፣ ያዳናቸውን አምላክ ረሱ፤ እርሱ ግን በካም ምድር ድንቅ ሥራ፣ በቀይ ባሕርም አስደናቂ ነገር አደረገ። ስለዚህ በመቅሠፍቱ እንዳያጠፋቸው ይመለስ ዘንድ፣ እርሱ የመረጠው ሙሴ በመካከል ገብቶ፣ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፣ እንደሚያጠፋቸው ተናግሮ ነበር።
መዝሙር 106 ያንብቡ
ያዳምጡ መዝሙር 106
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መዝሙር 106:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos