መዝሙር 105:16-45

መዝሙር 105:16-45 NASV

በምድሪቱ ላይ ራብን ጠራ፤ የምግብንም አቅርቦት ሁሉ አቋረጠ፤ በባርነት የተሸጠውን ሰው፣ ዮሴፍን ከእነርሱ አስቀድሞ ላከ። እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ፤ በዐንገቱም የብረት ማነቆ ገባ። የተናገረው ቃል እስኪፈጸምለት፣ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው። ንጉሥ ልኮ አስፈታው፤ የሕዝቦችም ገዥ ነጻ አወጣው። የቤቱ ጌታ፣ የንብረቱም ሁሉ አስተዳዳሪ አደረገው፤ ይኸውም ሹማምቱን በራሱ መንገድ ይመራ ዘንድ፣ ሽማግሌዎቹንም ጥበብ ያስተምር ዘንድ ነበር። እስራኤል ወደ ግብጽ ገባ፤ ያዕቆብ በካም ምድር መጻተኛ ሆነ። እግዚአብሔር ሕዝቡን እጅግ አበዛ፤ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው፤ ሕዝቡን እንዲጠሉ፣ በባሪያዎቹም ላይ እንዲያሤሩ ልባቸውን ለወጠ። ባሪያውን ሙሴን፣ የመረጠውንም አሮንን ላከ። እነርሱም ታምራታዊ ምልክቶችን በመካከላቸው፣ ድንቅ ነገሮቹንም በካም ምድር አደረጉ። ጨለማን ልኮ ምድሪቱን ጽልመት አለበሰ፤ እነርሱም በቃሉ ላይ ማመፅን ተዉ። ውሃቸውን ወደ ደም ለወጠ፤ ዓሦቻቸውንም ፈጀ። ምድራቸውም፣ የነገሥታታቸው እልፍኝ ሳይቀር፣ ጓጕንቸር ተርመሰመሰባቸው። እርሱ በተናገረ ጊዜ የዝንብ መንጋ መጣ፤ ትንኞችም ምድራቸውን ወረሩ። ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፤ ምድራቸውም ሁሉ መብረቅ አወረደ። ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፤ የአገራቸውንም ዛፍ ከተከተ። እርሱ በተናገረ ጊዜ አንበጣ መጣ፤ ስፍር ቍጥር የሌለውም ኵብኵባ ከተፍ አለ፤ የምድሪቱንም ዕፀዋት ሁሉ በላ፤ የመሬታቸውንም ፍሬ ሙጥጥ አደረገ፤ ደግሞም በአገራቸው ያለውን በኵር ሁሉ፣ የኀይላቸውንም ሁሉ በኵራት መታ። የእስራኤልንም ሕዝብ ብርና ወርቅ ጭኖ እንዲወጣ አደረገ፤ ከነገዶቻቸውም አንድም አልተደናቀፈም። እጅግ ፈርተዋቸው ነበርና፣ ወጥተው ሲሄዱ ግብጽ ደስ አላት። ደመናን እንደ መጋረጃ ዘረጋላቸው፤ እሳትም በሌሊት አበራላቸው። በለመኑትም ጊዜ፣ ድርጭት አመጣላቸው፤ የሰማይንም እንጀራ አጠገባቸው። ዐለቱን ሰነጠቀ፤ ውሃም ተንዶለደለ፤ እንደ ወንዝም በበረሓ ፈሰሰ። ለባሪያው ለአብርሃም የሰጠውን፣ ቅዱስ የተስፋ ቃሉን አስቧልና። ሕዝቡን በደስታ፣ ምርጦቹንም በእልልታ አወጣቸው። የሌሎችን ሕዝቦች ምድር ሰጣቸው፤ የእነዚህንም የድካም ፍሬ ወረሱ፤ ይህም ሥርዐቱን ይጠብቁ ዘንድ፣ ሕጉንም ይፈጽሙ ዘንድ ነው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}