የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ምሳሌ 19:8-23

ምሳሌ 19:8-23 NASV

ጥበብን ገንዘቡ የሚያደርጋት ነፍሱን ይወድዳል፤ ማስተዋልን የሚወድዳት ይሳካለታል። ሐሰተኛ ምስክር ከቅጣት አያመልጥም፤ ውሸት የሚነዛም ይጠፋል። ተላላ ተንደላቅቆ መኖር አይገባውም፤ ባሪያ የመሳፍንት ገዥ ከሆነማ የቱን ያህል ይከፋ! ጥበብ ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች፤ በደልን ንቆ መተውም መከበሪያው ነው። የንጉሥ ቍጣ እንደ አንበሳ ግሣት ነው፤ በፊቱ ሞገስ ማግኘትም በሣር ላይ እንዳለ ጠል ነው። ተላላ ልጅ ለአባቱ መጥፊያ ነው፤ ጨቅጫቃ ሚስትም እንደማያቋርጥ ጠፈጠፍ ናት። ቤትና ሀብት ከወላጆች ይወረሳሉ፤ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት። ስንፍና ከባድ እንቅልፍ ላይ ይጥላል፤ ዋልጌም ሰው ይራባል። ትእዛዞችን የሚያከብር ሕይወቱን ይጠብቃል፤ መንገዱን የሚንቅ ግን ይሞታል። ለድኻ የሚራራ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ ስላደረገውም ተግባር ዋጋ ይከፍለዋል። ገና ተስፋ ሳለ፣ ልጅህን ሥርዐት አስይዘው፤ ሲሞት ዝም ብለህ አትየው። ግልፍተኛ ሰው ቅጣትን መቀበል ይገባዋል፤ በምሕረት ካለፍኸው ሌላም ጊዜ አይቀርልህም። ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል፤ በመጨረሻም ጠቢብ ትሆናለህ። በሰው ልብ ብዙ ሐሳብ አለ፤ የሚፈጸመው ግን የእግዚአብሔር ሐሳብ ነው። ሰው የሚመኘው ጽኑ ፍቅር ነው፤ ውሸታም ከመሆንም ድኻ መሆን ይሻላል። እግዚአብሔርን መፍራት ወደ ሕይወት ይመራል፤ እንዲህ ያለውም ሰው እፎይ ብሎ ያርፋል፤ መከራም አያገኘውም።