ፊልጵስዩስ 2
2
ትሕትናን ከክርስቶስ መማር
1ከክርስቶስ ጋር ካላችሁ አንድነት የተነሣ የትኛውም መበረታታት፣ ከፍቅር የሆነ መጽናናት፣ የመንፈስ ኅብረት፣ ምሕረትና ርኅራኄ ካላችሁ፣ 2በአንድ ሐሳብ፣ በአንድ ፍቅር፣ በአንድ መንፈስና በአንድ ዐላማ በመሆን ደስታዬን ፍጹም አድርጉልኝ። 3ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ። 4እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ።
5በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይሁን፤
6እርሱ በባሕርዩ#2፥6 ወይም መልክ አምላክ ሆኖ ሳለ፣
ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቅቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤
7ነገር ግን የባሪያን መልክ#2፥7 ወይም ባሕርይ ይዞ፣
በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣
ራሱን ባዶ አደረገ፤
8ሰው ሆኖ ተገልጦም፣
ራሱን ዝቅ አደረገ፤
እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ
መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ።
9ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤
ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤
10ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣
ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣
11ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣
ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።
እንደ ከዋክብት ማብራት
12ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ሁልጊዜም ታዛዦች እንደ ነበራችሁ ሁሉ፣ አሁንም እኔ በአጠገባችሁ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም አሁን በሌለሁበት ጊዜ በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ 13እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።
14ማንኛውንም ነገር ሳታጕረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ 15ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው። 16የሕይወትንም ቃል ስታቀርቡ#2፥16 ስትይዙ፣ በከንቱ እንዳልሮጥሁ ወይም በከንቱ እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። 17ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቍርባን ብፈስስ እንኳ ከሁላችሁ ጋር ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ። 18እናንተም እንደዚሁ ከእኔ ጋር ደስ ልትሰኙና ሐሤት ልታደርጉ ይገባል።
ጢሞቴዎስና አፍሮዲጡ
19ስለ እናንተ ሰምቼ ደስ እንዲለኝ፣ ጢሞቴዎስን ቶሎ ወደ እናንተ ልልክላችሁ በጌታ ኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። 20ስለ እናንተ ደኅንነት ከልቡ የሚገድደው እንደ እርሱ ያለ ማንም የለኝም፤ 21ሁሉም የኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይሯሯጣሉና። 22ነገር ግን እንደምታውቁት ጢሞቴዎስ ማንነቱን አስመስክሯል፤ ልጅ ከአባቱ ጋር እንደሚያገለግል፣ ከእኔ ጋር በወንጌል ሥራ አገልግሏልና። 23እንግዲህ የራሴን የወደ ፊት ሁኔታ እንዳጣራሁ ልልከው ተስፋ አደርጋለሁ። 24እኔም ራሴ ቶሎ እንደምመጣ በጌታ ታምኛለሁ።
25እንዲሁም ወንድሜን፣ የሥራ ባለደረባዬንና አብሮኝ ወታደር የሆነውን፣ በሚያስፈልገኝ ሁሉ እንዲንከባከበኝ የላካችሁትን፣ የእናንተ መልእክተኛ የሆነውን አፍሮዲጡን መልሼ እንድልክላችሁ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። 26እርሱ ሁላችሁንም ይናፍቃልና፤ መታመሙን ስለ ሰማችሁም ተጨንቋል። 27በርግጥም ታምሞ ለሞት ተቃርቦ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ምሕረት አደረገለት፤ በሐዘን ላይ ሐዘን እንዳይደራረብብኝ ለእኔም ጭምር እንጂ ለእርሱ ብቻ አይደለም። 28ስለዚህ እርሱን እንደ ገና ስታዩ ደስ እንዲላችሁና የእኔም ጭንቀት እንዲቀልል ልልከው በጣም ጓጕቻለሁ። 29በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፤ እንደ እርሱ ያሉትንም ሰዎች አክብሯቸው። 30እርሱም እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት ለማሟላት ሲል ለሕይወቱ እንኳ ሳይሳሳ፣ ለክርስቶስ ሥራ ከሞት አፋፍ ደርሶ ነበርና።
Currently Selected:
ፊልጵስዩስ 2: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.