የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ፊልጵስዩስ 1

1
1የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋዮች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ፤
ከቤተ ክርስቲያን ኤጲስ ቆጶሳትና#1፥1 ወይም ተመልካች ጠባቂዎች ከዲያቆናት ጋር በፊልጵስዩስ ላሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ቅዱሳን ለሆኑ ሁሉ፤
2ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ምስጋናና ጸሎት
3እናንተን ባስታወስሁ ቍጥር አምላኬን አመሰግናለሁ። 4ዘወትር ስለ ሁላችሁ ስጸልይ፣ በደስታ እጸልያለሁ፤ 5ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ እስካሁን ድረስ በወንጌል አገልግሎት ተካፋይ ሆናችኋልና። 6በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ከፍጻሜው እንደሚያደርሰው ርግጠኛ ነኝ።
7በልቤ ስላላችሁ፣ ስለ ሁላችሁ እንዲህ ማሰቤ ተገቢ ነው፤ በእስራቴም ሆነ ለወንጌል ስመክትና ሳጸናው ሁላችሁም ከእኔ ጋር የእግዚአብሔር ጸጋ ተካፋዮች ናችሁና። 8በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያህል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው።
9ፍቅራችሁ በጥልቅ ዕውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ እጸልያለሁ። 10ይኸውም ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ እንድታውቁ፣ እስከ ክርስቶስም ቀን ድረስ ንጹሓንና ነቀፋ የሌለባችሁ እንድትሆኑ፣ 11ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ እንድትሞሉ ነው።
በጳውሎስ እስራት ወንጌል መስፋፋቱ
12አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ በእኔ ላይ የደረሰው ነገር ወንጌል በይበልጥ እንዲስፋፋ መርዳቱን ታውቁ ዘንድ እወድዳለሁ። 13ከዚህ የተነሣ እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንደ ሆነ፣ በቤተ መንግሥት ዘበኞችና#1፥13 ወይም በቤተ መንግሥት ሁሉ በሌሎችም ሁሉ ዘንድ ታውቋል። 14በእኔ መታሰር ምክንያት በጌታ ካሉት ወንድሞች ብዙዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሀት፣ በድፍረት ለመናገር ብርታት አግኝተዋል።
15አንዳንዶች ከቅናትና ከፉክክር የተነሣ፣ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ። 16እነዚህ፣ እኔ ለወንጌል ለመሟገት እዚህ እንዳለሁ ስለሚያውቁ፣ በፍቅር ይህን ያደርጋሉ፤ 17እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ ሳለሁ መከራ ሊያጸኑብኝ ዐስበው፣ በቅንነት ሳይሆን ለግል ምኞታቸው ሲሉ ክርስቶስን ይሰብካሉ#1፥16-17 አንዳንድ ጥንታዊ ያልሆኑ ቅጆች የ16 እና 17 ቅደም ተከተል ለዋውጠውታል።18ታዲያ ችግሩ ከምኑ ላይ ነው? ቁም ነገሩ በቅንነትም ይሁን በማስመሰል በማንኛውም መንገድ ክርስቶስ መሰበኩ ነው። በዚህም ደስ ይለኛል።
አዎን፤ ደስ ይለኛል፤ 19በእኔ ላይ የደረሰው ነገር፣ በጸሎታችሁ አማካይነትና ከኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በተሰጠ ረድኤት ለመዳኔ#1፥19 ወይም ለትድግናዬ እንደሚሆን ዐውቃለሁና። 20በምንም ዐይነት መንገድ ዐፍሬ እንዳልገኝ ጽኑ ናፍቆትና ተስፋ አለ፤ ነገር ግን እንደ ወትሮው ሁሉ ዛሬም በሕይወትም ሆነ በሞት ክርስቶስ በሥጋዬ እንዲከበር ሙሉ ድፍረት ይኖረኛል። 21ለእኔ፣ መኖር ክርስቶስ ነው፤ ሞትም ማትረፍ ነው። 22በሥጋ ከቈየሁ፣ ፍሬያማ ተግባር ይኖረኛል፤ ነገር ግን የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም። 23በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ፣ ከክርስቶስም ጋር ልሆን እናፍቃለሁ፤ ይህ እጅግ የተሻለ ነውና። 24ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ለእናንተ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። 25ይህን በማስተዋል፣ በእምነት እንድታድጉና ደስ እንዲላችሁ፣ በሁላችሁ ዘንድ እንደምቈይና እንደምኖር ተረድቻለሁ። 26እንደ ገና መጥቼ በእናንተ ዘንድ በምሆንበት ጊዜ፣ በእኔ ምክንያት በክርስቶስ ኢየሱስ ያላችሁ ደስታ ይበዛላችኋል።
27ብቻ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ፤ ይህ ከሆነ መጥቼ ባያችሁ ወይም በርቀት ሆኜ ስለ እናንተ ብሰማ፣ ለወንጌል እምነት እንደ አንድ ሰው ሆናችሁ በመጋደል በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ እንደምትቆሙ ዐውቃለሁ። 28በማንኛውም መንገድ በተቃዋሚዎቻችሁ አትሸበሩ፤ ይህ እነርሱ እንደሚጠፉ፣ እናንተ ግን እንደምትድኑ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ምልክት ነው። 29በክርስቶስ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን ስለ እርሱ መከራ እንድትቀበሉም ይህ ጸጋ ተሰጥቷችኋልና፤ 30ቀድሞ እንዳያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ በምትሰሙት በዚያው ዐይነት ተጋድሎ እናንተም እያለፋችሁ ነውና።

Currently Selected:

ፊልጵስዩስ 1: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ