ዘኍል 36
36
የሰለጰዓድ ሴት ልጆች ርስት
36፥1-12 ተጓ ምብ – ዘኍ 27፥1-11
1ከዮሴፍ ዝርያ ጐሣዎች የሆኑ የምናሴ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣ የገለዓድ ጐሣ የቤተ ሰብ አለቆች ወደ ሙሴና የእስራኤላውያን ቤተ ሰቦች አለቆች ወደ ሆኑት መሪዎች ቀርበው ተናገሩ፤ 2እንዲህም አሉ፤ “ምድሪቱን በዕጣ ከፋፍለህ ለእስራኤላውያን ርስት አድርገህ እንድትሰጣቸው እግዚአብሔር (ያህዌ) አንተን ጌታዬን ባዘዘ ጊዜ የወንድማችንን የሰለጰዓድን ድርሻ ለሴቶች ልጆቹ እንድትሰጥ አዝዞሃል። 3ከሌሎች የእስራኤል ነገዶች ባል ቢያገቡ ድርሻቸው ከእኛ የዘር ርስት ላይ ተወስዶ የሚያገቧቸው ሰዎች ላሉበት ነገድ ይተላለፋል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ በዕጣ ከተደለደለልን ርስት ላይ ከፊሉ ሊቀነስብን ነው። 4የእስራኤላውያን ዓመተ ኢዮቤልዩ በሚመጣበት ጊዜ የእነርሱ ድርሻ ወደ ባሎቻቸው ነገድ ይጨመራል፤ ይህ ከሆነም ድርሻቸው ከአባቶቻችን ነገድ ርስት ላይ ይወሰዳል።”
5ከዚህ በኋላ ሙሴ እግዚአብሔር (ያህዌ) በተናገረው መሠረት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “የዮሴፍ ነገድ የተናገረው ትክክል ነው፤ 6እንግዲህ የሰለጰዓድን ሴት ልጆች በተመለከተ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያዝዘው ይህ ነው፤ ከአባታቸው ነገድ ወገን እስከ ሆነ ድረስ የወደዱትን ማግባት ይችላሉ። 7እያንዳንዱ እስራኤላዊም ከቀደሙት አባቶቹ በወረሰው ርስት ይጽና፤ በእስራኤል ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ የሚተላለፍ ርስት አይኖርም። 8እያንዳንዱ እስራኤላዊ የየአባቶቹን ርስት መውረስ ስላለበት፣ በማንኛውም የእስራኤል ነገድ ውስጥ ርስት የምትወርስ የትኛዪቱም ሴት፣ ከአባቷ ነገድ ወገን የሆነውን አንዱን ማግባት አለባት። 9እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ የወረሰውን መሬት እንዳለ ማቈየት ስላለበት፣ ርስት ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ አይተላለፍም።”
10ስለዚህም የሰለጰዓድ ሴት ልጆች እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። 11የሰለጰዓድ ሴት ልጆች፤ ማህለህ፣ ቲርጻ፣ ዔግላ፣ ሚልካ፣ ኑዓ ከአባታቸው ወንድሞች ልጆች ጋር ተጋቡ። 12ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ዝርያ ጐሣዎች ጋር በመጋባታቸው፣ ርስታቸው በዚያው በአባታቸው ጐሣና ነገድ እጅ እንዳለ ቀረ።
13ከኢያሪኮ#36፥13 በዕብራይስጥ የኢያሪኮ ዮርዳኖስ የሚል ሲሆን፣ ይህም የዮርዳኖስ ወንዝ የጥንት ስም ሳይሆን አይቀርም። ማዶ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ፣ በሞዓብ ሜዳ ሳሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ትእዛዞችና ደንቦች እነዚህ ናቸው።
Currently Selected:
ዘኍል 36: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.