የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘኍል 31:25-54

ዘኍል 31:25-54 NASV

እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አንተ፣ ካህኑ አልዓዛርና በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ያሉት የየቤተ ሰቡ አለቆች ሆናችሁ የተማረከውን ሕዝብና እንስሳት ሁሉ ቍጠሩ። ምርኮውንም ለሁለት ከፍላችሁ በጦርነቱ ለተካፈሉት ወታደሮችና ለቀረው ማኅበረ ሰብ አከፋፍሉት። በጦርነቱ ከተካፈሉት ወታደሮች ድርሻ ላይ፣ ከሰውም ሆነ ከቀንድ ከብት፣ ከአህያ፣ ከበግ ወይም ከፍየል ከየአምስት መቶው አንዱን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ግብር አውጣ። ይህንም ግብር ከድርሻቸው ላይ ወስደህ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፈንታ በማድረግ ለካህኑ ለአልዓዛር ስጠው። ከእስራኤላውያን እኩሌታ ድርሻ ደግሞ ከሰውም ይሁን ከቀንድ ከብት፣ ከአህያ፣ ከበግ፣ ከፍየል ወይም ከሌሎች እንስሳት ከየአምሳው አንዳንድ መርጠህ፣ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ማደሪያ ድንኳን በኀላፊነት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ስጣቸው።” ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። ወታደሮቹ ማርከው ከወሰዱለት ምርኮ ውስጥ የቀረው ይህ ነበር፤ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺሕ በግ፣ ሰባ ሁለት ሺሕ የቀንድ ከብት፣ ስድሳ አንድ ሺሕ አህያ ወንድ ያላወቁ ሠላሳ ሁለት ሺሕ ሴቶች። በጦርነቱ ላይ የነበሩት ወታደሮች እኩሌታ ድርሻ ይህ ነበር፤ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺሕ አምስት መቶ በግ፣ ከእነዚህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠ ግብር ስድስት መቶ ሰባ አምስት ነበር። ሠላሳ ስድስት ሺሕ የቀንድ ከብት፣ ከእነዚህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠው ግብር ሰባ ሁለት ነበር። ሠላሳ ሺሕ አምስት መቶ አህያ፣ ከእነዚህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠው ግብር ስድሳ አንድ ነበር። ዐሥራ ስድስት ሺሕ ሰው፣ ከእነዚህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠው ግብር ሠላሳ ሁለት ነበር። ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው የእግዚአብሔር (ያህዌ) ድርሻ የሆነውን ግብር ለአልዓዛር ሰጠው። ሙሴ ከዘመቱት ሰዎች የለየው የእስራኤላውያን እኩሌታ ድርሻ ማለትም፣ የማኅበረ ሰቡ ድርሻ ይህ ነበር፤ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺሕ አምስት መቶ በግ፣ ሠላሳ ስድስት ሺሕ የቀንድ ከብት፣ ሠላሳ ሺሕ አምስት መቶ አህያ፣ ዐሥራ ስድስት ሺሕ ሰው። ከእስራኤላውያን እኩሌታ ድርሻ ላይ፣ ሙሴ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው ከየአምሳው ሰውና እንስሳ አንዳንድ መርጦ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ማደሪያ ድንኳን በኀላፊነት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ሰጣቸው። ከዚያም በኋላ በሰራዊቱ ክፍሎች ላይ የተሾሙት የሻለቆችና የመቶ አለቆች ወደ ሙሴ ቀርበው፣ እንዲህ አሉት፤ “እኛ አገልጋዮችህ በእጃችን ሥር ያሉትን ወታደሮች ቈጥረናል፤ አንድም የጐደለ የለም። ስለዚህ እያንዳንዳችን ያገኘነውን የወርቅ ጌጣጌጥ፣ የእግር ዐልቦዎች፣ የእጅ አንባሮች፣ የጣት ቀለበቶች፣ የጆሮ ጕትቻዎችና የዐንገት ሐብሎች በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ማስተስረያ እንዲሆነን መባ አድርገን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አምጥተናል።” ሙሴና ካህኑ አልዓዛር በጌጣጌጥ መልክ የተሠራውን ወርቅ ሁሉ ተቀበሏቸው። ሙሴና አልዓዛር ከሻለቆቹና ከመቶ አለቆቹ በመቀበል ስጦታ አድርገው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቀረቡት ወርቅ ዐሥራ ስድስት ሺሕ ሰባት መቶ አምሳ ሰቅል መዘነ። እያንዳንዱም ወታደር ለራሱ የወሰደው ምርኮ ነበረው። ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ወርቁን ከሻለቆቹና ከመቶ አለቆቹ ተቀብለው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለእስራኤላውያን መታሰቢያ እንዲሆን ወደ መገናኛው ድንኳን አመጡት።