“ ‘በየወሩ መባቻ እንከን የሌለባቸውን ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግ፣ ዓመት የሆናቸውን ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ። ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋር ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ ልም ዱቄት፣ ከአውራውም በግ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቀርባል፤ እንደዚሁም ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋር ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አቅርቡ፤ ይህም ለሚቃጠል መሥዋዕት ሲሆን ሽታው ደስ የሚያሰኝና በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርብ መሥዋዕት ነው። ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋር ለመጠጥ ቍርባን የሚሆን የኢን ግማሽ የወይን ጠጅ፣ ከአውራው በግ ጋር የኢን አንድ ሦስተኛ፣ ከእያንዳንዱም የበግ ጠቦት ጋር የኢን አንድ አራተኛ የወይን ጠጅ ይቅረብ፤ ይህም በየወሩ መባቻ ዓመቱን ሙሉ የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። ከመጠጥ ቍርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት ሆኖ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ይቀርባል። “ ‘የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፋሲካ በዓል ይከበራል። በዚሁ ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን በዓል ይሆናል፤ እስከ ሰባትም ቀን ድረስ ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ብሉ። በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባራችሁንም አትሥሩበት። እንከን የሌለባቸው ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ። ከእያንዳንዱም ወይፈን ጋር ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ ልም ዱቄት፣ ከአውራውም በግ ጋር የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት አቅርቡ፤ ከሰባቱም የበግ ጠቦቶች ከእያንዳንዳቸው ጋር የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አዘጋጁ። በተጨማሪም ማስተስረያ እንዲሆናችሁ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ። እነዚህንም ጧት ጧት በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር አቅርቧቸው። በዚህም ዐይነት ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሆኖ በየዕለቱ ለሰባት ቀን በእሳት ለሚቀርብ መሥዋዕት የምግብ ቍርባን አዘጋጁ፤ ይህም ከመጠጥ ቍርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ሆኖ በተጨማሪ ይቀርባል። በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባርም አትሥሩበት። “ ‘በየሳምንቱ በሚደረገው በዓል፣ አዲስ የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምታቀርቡበት በፍሬ በኵራት ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባርም አትሥሩበት። ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸውን ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ አድርጋችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ። ከእያንዳንዱም ወይፈን ጋር ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፉ ሦስት ዐሥረኛ፣ ከአውራው በግ ጋር የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቀርባል፤ ከሰባቱም የበግ ጠቦቶች ከእያንዳንዳቸው ጋር የኢፉ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቅረብ። በተጨማሪም ማስተስረያ እንዲሆንላችሁ አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ። ከእህል ቍርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት በተጨማሪ፣ እነዚህን ከመጠጥ ቍርባናቸው ጋር አቅርቡ። እንስሳቱም እንከን የሌላቸው መሆናቸውን አረጋግጡ።
ዘኍል 28 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘኍል 28
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘኍል 28:11-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos