እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ መካከል በመሪነትና በእልቅና ብቃት አላቸው የምትላቸውን ሰባ የእስራኤል ሽማግሌዎች አምጣልኝ፤ ካንተም ጋራ ይቆሙ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን እንዲመጡ አድርግ። ወደዚያም ወርጄ አነጋግርሃለሁ፤ ባንተ ላይ ካለው መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ የሕዝቡንም ሸክም ብቻህን እንዳትሸከም እነርሱ ያግዙሃል። “ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ነገ ሥጋ ትበላላችሁና ራሳችሁን በመቀደስ ተዘጋጁ። “በግብጽ ተመችቶን ነበር፤ አሁን ግን ሥጋ ማን ይሰጠናል!” ብላችሁ ያለቀሳችሁትን እግዚአብሔር ሰምቷል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ሥጋ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ትበላላችሁ። የምትበሉትም ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ወይም ለዐምስት፣ ለዐሥር ወይም ለሃያ ቀን አይደለም፤ ነገር ግን በአፍንጫችሁ እስኪወጣና እስኪያንገፈግፋችሁ ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ፤ በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችሁ በፊቱ፣ “ለምን ከግብጽ ወጣን?” ብላችሁ አልቅሳችኋልና።’ ” ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እነሆ እኔ በስድስት መቶ ሺሕ እግረኛ መካከል እገኛለሁ፤ አንተ ደግሞ ‘ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ’ ብለሃል፤ ታዲያ ስንት የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋ ቢታረድላቸው ይበቃ ይሆን? በባሕር ያለው ዓሣ ሁሉ ቢያዝ ሊዳረሳቸው ይችላልን?” እግዚአብሔርም ለሙሴ፣ “በውኑ የእግዚአብሔር ክንድ ይህን ያህል ዐጭር ነውን? የነገርሁህ ቃል እውነት መሆን አለመሆኑን አሁኑኑ ታየዋለህ” ሲል መለሰለት። ሙሴም ወጣና እግዚአብሔር ያለውን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ ከሕዝቡም ሽማግሌዎች ሰባውን ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረጋቸው። ከዚያም እግዚአብሔር በደመና ወርዶ ተናገረው፤ በሙሴ ላይ ከነበረውም መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈሱ ባደረባቸውም ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልደገሙትም። ኤልዳድና ሞዳድ የተባሉ ሁለት ሰዎች ግን ሰፈር ውስጥ ቀርተው ነበር፤ እነርሱም ከሽማግሌዎቹ ጋራ ተቈጥረው ሳለ ወደ ድንኳኑ አልሄዱም ነበር፤ ሆኖም መንፈስ በእነርሱም ላይ ስላደረባቸው ሰፈር ውስጥ እያሉ ትንቢት ተናገሩ። አንድ ወጣትም ሮጦ በመሄድ፣ “ኤልዳድና ሞዳድ ሰፈር ውስጥ ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ ለሙሴ ነገረው። ከወጣትነቱ ጀምሮ የሙሴ ረዳት የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱም ተነሥቶ፣ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ፤ ከልክላቸው እንጂ” ሲል ተናገረ። ሙሴ ግን መልሶ፣ “ስለ እኔ ቀንተህ ነውን? የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፣ እግዚአብሔርም መንፈሱን ቢያሳድርባቸው ምንኛ ደስ ባለኝ!” አለ፤ ከዚያም ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ሰፈር ተመለሱ። በዚህ ጊዜ ነፋስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥቶ ድርጭቶችን ከባሕር ወደ ሰፈር አመጣ፤ በየአቅጣጫውም ከፍታው ሁለት ክንድ፣ ርቀቱም የአንድ ቀን መንገድ ያህል እስኪሆን ድረስ በሰፈሩ ዙሪያ ከመራቸው። በዚያ ዕለት ቀንና ሌሊቱን በሙሉ፣ በማግስቱም ሙሉውን ቀን እንደዚሁ ሕዝቡ ወጥቶ ድርጭቶች ሰበሰበ፤ ከዐሥር የቆሮስ መስፈሪያ ያነሰ የሰበሰበ ማንም አልነበረም፤ የሰበሰቡትንም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ አሰጡት። ነገር ግን ሥጋው ገና በጥርስና በጥርሳቸው መካከል ሳለ አላምጠው ሳይውጡት የእግዚአብሔር ቍጣ በላያቸው ነደደ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት ክፉኛ መታ።
ዘኍልቍ 11 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘኍልቍ 11
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘኍልቍ 11:16-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች