ሰንባላጥ ቅጥሩን እንደምንሠራ በሰማ ጊዜ ተቈጣ፤ እጅግም ተበሳጨ። በአይሁድም ላይ ተሣለቀ፤ በተባባሪዎቹና በሰማርያ ሰራዊት ፊት፣ “እነዚህ ደካማ አይሁድ ምን እያደረጉ ነው? ቅጥራቸውን መልሰው ሊሠሩ ነውን? መሥዋዕት ሊያቀርቡ ነውን? በአንዲት ጀንበር ሠርተው ሊጨርሱ ነውን? እንደዚያ ተቃጥሎ የፍርስራሽ ክምር የሆነውን ድንጋይ ነፍስ ሊዘሩበት ይችላሉን?” አለ። በአጠገቡም ቆሞ የነበረው አሞናዊው ጦቢያ፣ “ለመሆኑ የሚገነቡት ምንድን ነው? በድንጋይ የሚሠሩት ቅጥር እኮ ቀበሮ እንኳ ብትወጣበት ሊፈርስ ይችላል” አለ። አምላካችን ሆይ፤ ተንቀናልና ስማን፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ አውርድባቸው፤ በምርኮ ምድር እንዲበዘበዙ አሳልፈህ ስጣቸው። የፈረሰውን በሚሠሩት ፊት የስድብ ናዳ አውርደዋልና በደላቸውን ይቅር አትበል፤ ኀጢአታቸውንም ከፊትህ አታጥፋው። ሕዝቡ ከልቡ ስለሚሠራ፣ ቅጥሩን እኩሌታው ድረስ መልሰን ሠራነው። ሰንባላጥ፣ ጦቢያ፣ ዐረቦች፣ የአሞንና የአሽዶድ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌም ቅጥር ሥራ እየተፋጠነና ክፍት ቦታዎቹም ሁሉ እየተሞሉ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉ ዘንድ፣ ሽብርንም ይፈጥሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት አደሙ። እኛ ግን ወደ እግዚአብሔር ጸለይን፤ ዛቻቸውንም ለመቋቋም ቀንና ሌሊት የሚጠብቁ ዘቦችን መደብን። በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሕዝብ፣ “የሠራተኞቹ ጕልበት እየደከመ ነው፤ ከፍርስራሹም ብዛት የተነሣ ቅጥሩን መልሰን ለመሥራት አንችልም” አሉ። ጠላቶቻችን ደግሞ፣ “በመካከላቸው ገብተን እስክንገድላቸውና ሥራውን እስክናስቆም ድረስ አያውቁም ወይም አያዩም” አሉ። ከዚያም በአጠገባቸው የሚኖሩ አይሁድ መጥተው፣ “እናንተ የትም ቦታ ብትሆኑ፣ እኛን ማጥቃታቸው አይቀርም!” በማለት ዐሥር ጊዜ ደጋግመው ነገሩን። ስለዚህ ከቅጥሩ በስተ ኋላ በሚገኙ ግልጽ ቦታዎች ላይ ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ሰይፋቸውን፣ ጦራቸውንና ቀስታቸውን እንደ ያዙ በየቤተ ሰባቸው በመመደብ ቦታቸውን እንዲይዙ አደረግሁ። ነገሩን በጥሞና ከተመለከትሁ በኋላ መኳንንቱን፣ ሹማምቱና የቀረውን ሕዝብ፣ “አትፍሯቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፤ ስለ ወንድሞቻችሁ፣ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ስለ ሚስቶቻችሁና ስለ ቤት ንብረታችሁ ተዋጉ” አልኋቸው። አድማቸውን እንዳወቅንባቸውና እግዚአብሔርም ዕቅዳቸውን ከንቱ እንዳደረገባቸው ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፣ ሁላችን ወደ ቅጥሩ፣ እያንዳንዳችንም ወደየሥራችን ተመለስን። ከዚያን ቀን ጀምሮ ከሰዎቼ እኩሌቶቹ ሥራውን ሠሩ፤ የቀሩት ደግሞ ጋሻና ጦር፣ ቀስትና ጥሩር ይዘው ነበር። የጦር አለቆች ከመላው የይሁዳ ሕዝብ በስተ ኋላ ቆሙ፤ እነርሱም ቅጥሩን ይገነቡ ነበር፤ ዕቃ የሚሸከሙት በአንድ እጃቸው ሥራቸውን ሲሠሩ፣ በሌላው እጃቸው የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ነበር፤ እያንዳንዱም ግንበኛ ቅጥሩን በሚሠራበት ጊዜ ሰይፉን በወገቡ ላይ ታጥቆ ነበር፤ መለከት የሚነፋው ሰው ግን ከእኔ አይለይም ነበር። ከዚያም ለመኳንንቱ፣ ለሹማምቱና ለቀረው ሕዝብ እንዲህ አልሁ፤ “ሥራው ታላቅ ነው፤ ብዙም ነው፤ እርስ በርሳችን በቅጥሩ ላይ እጅግ ተራርቀናል፤ የመለከት ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ፣ ወደ እኛ ተሰብሰቡ። አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል።” ስለዚህ ጎሕ ሲቀድ ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ እኩሌቶቹ ሰዎች ጦራቸውን እንደ ያዙ ሥራውን ቀጠልን። በዚያን ጊዜ ለሕዝቡ፣ “ሌሊት ዘብ በመጠበቅና ቀን ሥራ በመሥራት እንዲያገለግለን እያንዳንዱ ሰው ከነረዳቱ በኢየሩሳሌም ይቈይ” አልኋቸው። እኔም ሆንሁ ወንድሞቼ፣ ሰዎቼም ሆኑ ከእኔ ጋር ያሉት ጠባቂዎች ልብሳችንን አላወለቅንም፤ ለውሃ እንኳ በምንሄድበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የጦር መሣሪያውን እንደ ያዘ ነበር።
ነህምያ 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ነህምያ 4
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ነህምያ 4:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos