ማርቆስ 9:1-13

ማርቆስ 9:1-13 NASV

ቀጥሎም፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መካከል የእግዚአብሔር መንግሥት በኀይል ስትመጣ እስከሚያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ” አላቸው። ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን አስከትሎ ወደ አንድ ረዥም ተራራ ይዟቸው ወጣ፤ ብቻቸውንም ነበሩ። በፊታቸውም ተለወጠ፤ ልብሱም በምድር ላይ ማንም ዐጣቢ ዐጥቦ ሊያነጣው በማይችልበት ሁናቴ እጅግ ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ከኢየሱስ ጋራ ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፣ እዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚናገረውን አያውቅም ነበር። ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “ይህ የምወድደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ። ወዲያውም ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም ዐብሯቸው አልነበረም። ከተራራው በመውረድ ላይ ሳሉ፣ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። እነርሱም የተናገራቸውን ቃል በልባቸው አሳደሩት፤ ነገር ግን፣ “ከሙታን መነሣት” ምን ማለት እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ከዚያም፣ “ጸሐፍት አስቀድሞ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ለምን ይላሉ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ አስቀድሞ መጥቶ ሁሉንም ነገር ወደ ነበረበት ይመልሳል፤ ታዲያ፣ የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበልና መናቅ እንዳለበት የተጻፈው ለምን ይመስላችኋል? ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስማ መጥቶ ነበር፤ እነርሱም ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት የፈለጉትን ሁሉ አድርገውበታል።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች