የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 5

5
አጋንንት ያደሩበት ሰው መፈወሱ
5፥1-17 ተጓ ምብ – ማቴ 8፥28-34ሉቃ 8፥26-37
5፥18-20 ተጓ ምብ – ሉቃ 8፥3839
1ባሕሩን ተሻግረው ጌራሴኖን#5፥1 አንዳንድ ቅጆች ደግሞ ጌርጌሴኖን ይላሉ። ወደ ተባለ አገር መጡ። 2ኢየሱስ ከጀልባ እንደ ወረደ፣ ርኩስ#5፥2 ወይም ክፉ፤ እንዲሁም 8 እና 13 ይመ መንፈስ ያደረበት ሰው ከመቃብር ቦታ ወጥቶ ሊገናኘው ወደ እርሱ መጣ። 3ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ውስጥ የሚኖርና ማንም በሰንሰለት እንኳ ሊያስረው የማይችል ነበር። 4ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበር፤ ነገር ግን የእጅ ሰንሰለቱን ይበጥስ፣ የእግር ብረቱንም ይሰብር ነበር። ማንም ይዞ ሊያቈየው የሚችል አልነበረም።
5በመቃብሮቹና በተራራዎቹ መካከል ቀንና ሌሊት እየተዘዋወረ በመጮኽ ሰውነቱን በድንጋይ ይቈራርጥ ነበር።
6ይህም ሰው ኢየሱስን ከሩቅ ባየው ጊዜ ወደ እርሱ ሮጦ ከፊቱ ተንበርክኮ ሰገደለት፤ 7በታላቅ ድምፅ ጮኾም፣ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ምን አለህ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር ይዤሃለሁ” አለው። 8ይህንም ያለው ኢየሱስ፣ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎት ስለ ነበር ነው።
9ከዚያም ኢየሱስ፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው።
“ብዙ ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው” አለው። 10ከአገር እንዳያስወጣቸውም አጥብቆ ለመነው።
11በአቅራቢያውም በሚገኝ ኰረብታ ላይ ትልቅ የዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር። 12ርኩሳን መናፍስቱም ኢየሱስን፣ “ወደ ዐሣማዎቹ ስደደን፤ እንድንገባባቸውም ፍቀድልን” ብለው ለመኑት። 13እርሱም ፈቀደላቸው። ርኩሳን መናፍስቱም ወጥተው በዐሣማዎቹ ገቡባቸው፤ ሁለት ሺሕ ያህል ዐሣማዎችም በገደሉ አፋፍ በመንደርደር ቍልቍል ወርደው በባሕር ውስጥ ሰጠሙ።
14እረኞቹ ሸሽተው ሄዱ፤ ወሬውን በከተማና በገጠር አዳረሱት፤ ሕዝቡም የሆነውን ለማየት ካለበት ወጣ። 15ወደ ኢየሱስም በመጡ ጊዜ፣ የአጋንንት ሰራዊት ዐድረውበት የነበረው ሰው፣ ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት በዚያ ተቀምጦ አዩት፤ ፈሩም። 16ይህን ያዩ ሰዎችም አጋንንት ስላደረበት ሰው የተደረገውንና ስለ ዐሣማዎቹም ለሕዝቡ አወሩ። 17ከዚያም ሕዝቡ አገራቸውን ለቅቆ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ይለምኑት ጀመር።
18ኢየሱስ ወደ ጀልባዪቱ በሚገባበት ጊዜ፣ አጋንንት ዐድሮበት የነበረው ሰው አብሮት ለመሄድ ለመነው። 19ኢየሱስ አልፈቀደለትም፤ ነገር ግን፣ “ወደ ቤትህ ሂድ፣ ለዘመዶችህም ጌታ ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና ያሳየህን ምሕረት ንገራቸው” አለው። 20ሰውየውም ሄደ፤ ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር ሁሉ ዐሥር ከተማ#5፥20 ዐሥር ከተማ የሚባለውን አካባቢ ግሪኩ ዴካፖሊስ ይለዋል። በተባለው አገር ያወራ ጀመር፤ የሰሙትም ሁሉ ተደነቁ።
የሞተችው ልጅና የታመመችው ሴት
5፥22-43 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥18-26ሉቃ 8፥41-56
21ኢየሱስ እንደ ገና በጀልባ ወደ ማዶ በተሻገረ ጊዜ፣ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰባሰበ፤ በባሕሩ ዳርቻም እንዳለ፣ 22ከምኵራብ አለቆች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለው ወደዚያ መጥቶ ስለ ነበር፣ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቆ፣ 23“ትንሿ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናትና ድና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት አጥብቆ ለመነው። 24ኢየሱስም አብሮት ሄደ።
ብዙ ሕዝብም ዙሪያውን እያጨናነቀው ተከተለው። 25ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረችም ሴት በዚያ ነበረች፤ 26በብዙ ባለ መድኀኒቶች ዘንድ በመንከራተት ያላትን ሁሉ ብትጨርስም፣ ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም ነበር። 27ስለ ኢየሱስም በሰማች ጊዜ፣ ከበስተ ኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ነካች፤ 28ምክንያቱም፣ “እንደ ምንም ብዬ ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” የሚል እምነት ነበራት። 29የሚፈስሰው ደሟ ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሥቃይዋ መገላገሏም በሰውነቷ ታወቃት።
30ወዲያውኑ ኢየሱስ፣ ኀይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐውቆ፤ ወደ ሕዝቡ ዘወር በማለት፣ “ልብሴን የነካው ማን ነው?” አለ።
31ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሕዝቡ ተጨናንቆ ሲጋፋህ እያየህ፣ ‘ማን ነው የነካኝ?’ እንዴት ትላለህ?” አሉት።
32ኢየሱስ ግን ይህን ያደረገው ማን እንደ ሆነ ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ። 33ሴትዮዋም ምን እንደ ተደረገላት ባወቀች ጊዜ እየፈራችና እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። 34እርሱም፣ “ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ዕረፊ” አላት።
35ኢየሱስም በመነጋገር ላይ እያለ፣ ሰዎች ከምኵራቡ አለቃ ከኢያኢሮስ ቤት መጥተው፣ “ልጅህ ሞታለች፤ ከእንግዲህ መምህሩን ለምን ታደክመዋለህ?” አሉት።
36ኢየሱስ ግን ሰዎቹ የተናገሩትን ችላ በማለት የምኵራቡን አለቃ፣ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፤” አለው።
37ከጴጥሮስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። 38ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤት እንደ ደረሱ፣ ኢየሱስ ግርግሩንና ሰዎቹም ዋይ ዋይ እያሉ አምርረው ሲያለቅሱ ተመለከተ። 39ወደ ቤትም ገብቶ፣ “ይህ ሁሉ ግርግርና ልቅሶ ምንድን ነው? ብላቴናዪቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። 40ሰዎቹ ግን ሣቁበት።
ሰዎቹን ሁሉ ከቤት ካስወጣ በኋላ፣ የብላቴናዪቱን አባትና እናት እንዲሁም አብረውት የመጡትን ደቀ መዛሙርት አስከትሎ ብላቴናዪቱ ወዳለችበት ገባ። 41ከዚያም የብላቴናዪቱን እጅ ይዞ፣ “ጣሊታ ቁሚ!” አላት፤ ትርጕሙም፣ “አንቺ ልጅ ተነሺ” ማለት ነው። 42ብላቴናዪቱም ወዲያውኑ ተነሥታ ቆመች፤ ወዲያ ወዲህም ሄደች። ዕድሜዋም ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር። ሰዎቹም በሁኔታው እጅግ ተደነቁ። 43እርሱም ይህን ነገር ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ የሚበላ ነገር እንዲሰጧትም ነገራቸው።

Currently Selected:

ማርቆስ 5: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ