ኢየሱስ እንደ ገና በጀልባ ወደ ማዶ በተሻገረ ጊዜ፣ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰባሰበ፤ በባሕሩ ዳርቻም እንዳለ፣ ከምኵራብ አለቆች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለው ወደዚያ መጥቶ ስለ ነበር፣ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቆ፣ “ትንሿ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናትና ድና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት አጥብቆ ለመነው። ኢየሱስም አብሮት ሄደ። ብዙ ሕዝብም ዙሪያውን እያጨናነቀው ተከተለው። ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረችም ሴት በዚያ ነበረች፤ በብዙ ባለ መድኀኒቶች ዘንድ በመንከራተት ያላትን ሁሉ ብትጨርስም፣ ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም ነበር። ስለ ኢየሱስም በሰማች ጊዜ፣ ከበስተ ኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ነካች፤ ምክንያቱም፣ “እንደ ምንም ብዬ ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” የሚል እምነት ነበራት። የሚፈስሰው ደሟ ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሥቃይዋ መገላገሏም በሰውነቷ ታወቃት። ወዲያውኑ ኢየሱስ፣ ኀይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐውቆ፤ ወደ ሕዝቡ ዘወር በማለት፣ “ልብሴን የነካው ማን ነው?” አለ። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሕዝቡ ተጨናንቆ ሲጋፋህ እያየህ፣ ‘ማን ነው የነካኝ?’ እንዴት ትላለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን ይህን ያደረገው ማን እንደ ሆነ ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ። ሴትዮዋም ምን እንደ ተደረገላት ባወቀች ጊዜ እየፈራችና እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። እርሱም፣ “ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ዕረፊ” አላት። ኢየሱስም በመነጋገር ላይ እያለ፣ ሰዎች ከምኵራቡ አለቃ ከኢያኢሮስ ቤት መጥተው፣ “ልጅህ ሞታለች፤ ከእንግዲህ መምህሩን ለምን ታደክመዋለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን ሰዎቹ የተናገሩትን ችላ በማለት የምኵራቡን አለቃ፣ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፤” አለው። ከጴጥሮስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤት እንደ ደረሱ፣ ኢየሱስ ግርግሩንና ሰዎቹም ዋይ ዋይ እያሉ አምርረው ሲያለቅሱ ተመለከተ። ወደ ቤትም ገብቶ፣ “ይህ ሁሉ ግርግርና ልቅሶ ምንድን ነው? ብላቴናዪቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። ሰዎቹ ግን ሣቁበት። ሰዎቹን ሁሉ ከቤት ካስወጣ በኋላ፣ የብላቴናዪቱን አባትና እናት እንዲሁም አብረውት የመጡትን ደቀ መዛሙርት አስከትሎ ብላቴናዪቱ ወዳለችበት ገባ። ከዚያም የብላቴናዪቱን እጅ ይዞ፣ “ጣሊታ ቁሚ!” አላት፤ ትርጕሙም፣ “አንቺ ልጅ ተነሺ” ማለት ነው። ብላቴናዪቱም ወዲያውኑ ተነሥታ ቆመች፤ ወዲያ ወዲህም ሄደች። ዕድሜዋም ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር። ሰዎቹም በሁኔታው እጅግ ተደነቁ። እርሱም ይህን ነገር ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ የሚበላ ነገር እንዲሰጧትም ነገራቸው።
ማርቆስ 5 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 5
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 5:21-43
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos