ባሕሩን ተሻግረው ጌርጌሴኖን ወደሚባል አገር መጡ። ኢየሱስ ከጀልባ እንደ ወረደ፣ ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ከመቃብር ቦታ ወጥቶ ሊገናኘው ወደ እርሱ መጣ። ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ውስጥ የሚኖርና ማንም በሰንሰለት እንኳ ሊያስረው የማይችል ነበር። ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበር፤ ነገር ግን የእጅ ሰንሰለቱን ይበጥስ፣ የእግር ብረቱንም ይሰብር ነበር። ማንም ይዞ ሊያቈየው የሚችል አልነበረም። በመቃብሮቹና በተራሮቹ መካከል ቀንና ሌሊት እየተዘዋወረ በመጮኽ ሰውነቱን በድንጋይ ይቈራርጥ ነበር። ይህም ሰው ኢየሱስን ከሩቅ ባየው ጊዜ ወደ እርሱ ሮጦ ከፊቱ ተንበርክኮ ሰገደለት፤ በታላቅ ድምፅ ጮኾም፣ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ምን አለህ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር ይዤሃለሁ!” አለው። ይህንም ያለው ኢየሱስ፣ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎት ስለ ነበር ነው። ከዚያም ኢየሱስ፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። “ብዙ ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው” አለው። እርሱም ከአገር እንዳያስወጣቸውም አጥብቆ ለመነው። በአቅራቢያውም በሚገኝ ኰረብታ ላይ ትልቅ የዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር። ርኩሳን መናፍስቱም ኢየሱስን፣ “ወደ ዐሣማዎቹ ስደደን፤ እንድንገባባቸውም ፍቀድልን” ብለው ለመኑት። እርሱም ፈቀደላቸው። ርኩሳን መናፍስቱም ወጥተው በዐሣማዎቹ ገቡባቸው፤ ሁለት ሺሕ ያህል ዐሣማዎችም በገደሉ አፋፍ በመንደርደር ቍልቍል ወርደው በባሕር ውስጥ ሰጠሙ። እረኞቹ ሸሽተው ሄዱ፤ ወሬውን በከተማና በገጠር አዳረሱት፤ ሕዝቡም የሆነውን ለማየት ካለበት ወጣ። ወደ ኢየሱስም በመጡ ጊዜ፣ የአጋንንት ሰራዊት ሌጌዎን ዐድረውበት የነበረው ሰው፣ ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት በዚያ ተቀምጦ አዩት፤ ፈሩም። ይህን ያዩ ሰዎችም አጋንንት ላደሩበት ሰው የሆነውንና ስለ ዐሣማዎቹም ለሕዝቡ አወሩ። ከዚያም አገራቸውን ለቅቆ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ይለምኑት ጀመር። ኢየሱስ ወደ ጀልባዪቱ በሚገባበት ጊዜ፣ አጋንንት ዐድረውበት የነበረው ሰው ዐብሮት ለመሆን ለመነው። ኢየሱስ አልፈቀደለትም፤ ነገር ግን፣ “ወደ ቤትህ ሂድ፣ ለዘመዶችህም ጌታ ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና ያሳየህን ምሕረት ንገራቸው” አለው። ሰውየውም ሄደ፤ ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር ሁሉ ዐሥር ከተማ በተባለው አገር ያወራ ጀመር፤ የሰሙትም ሁሉ ተደነቁ። ኢየሱስ እንደ ገና በጀልባ ወደ ማዶ በተሻገረ ጊዜ፣ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰባሰበ፤ በባሕሩ ዳርቻም እንዳለ፣ ከምኵራብ አለቆች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለው ወደዚያ መጥቶ ስለ ነበር፣ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሮቹ ላይ ወድቆ፣ “ትንሿ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናትና ድና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት አጥብቆ ለመነው። ኢየሱስም ዐብሮት ሄደ። ብዙ ሕዝብም ዙሪያውን እያጨናነቀው ተከተለው። ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች አንዲት ሴት በዚያ ነበረች፤ በብዙ ባለመድኀኒቶች ዘንድ በመንከራተት ያላትን ሁሉ ብትጨርስም፣ ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም ነበር። ስለ ኢየሱስም በሰማች ጊዜ፣ ከበስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ነካች፤ ምክንያቱም፣ “እንደ ምንም ብዬ ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” የሚል እምነት ነበራት። የሚፈስሰው ደሟም ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሥቃይዋ መገላገሏም በሰውነቷ ታወቃት። ወዲያውኑ ኢየሱስ፣ ኀይል ከርሱ እንደ ወጣ ዐውቆ፤ ወደ ሕዝቡ ዘወር በማለት፣ “ልብሴን የነካው ማን ነው?” አለ። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሕዝቡ ተጨናንቆ ሲጋፋህ እያየህ፣ ‘ማን ነው የነካኝ?’ እንዴት ትላለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን ይህን ያደረገው ማን እንደ ሆነ ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ። ሴትዮዋም ምን እንደ ተደረገላት ባወቀች ጊዜ እየፈራችና እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። እርሱም፣ “ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ዕረፊ” አላት። ኢየሱስም በመነጋገር ላይ እያለ፣ ሰዎች ከምኵራቡ አለቃ ከኢያኢሮስ ቤት መጥተው፣ “ልጅህ ሞታለች፤ ከእንግዲህ መምህሩን ለምን ታደክመዋለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን ሰዎቹ የተናገሩትን ችላ በማለት የምኵራቡን አለቃ፣ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፤” አለው። ከጴጥሮስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤት እንደ ደረሱ፣ ኢየሱስ ግርግሩንና ሰዎቹም ዋይ ዋይ እያሉ አምርረው ሲያለቅሱ ተመለከተ። ወደ ቤትም ገብቶ፣ “ይህ ሁሉ ግርግርና ልቅሶ ምንድን ነው? ብላቴናዪቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። ሰዎቹ ግን ሣቁበት። ሰዎቹን ሁሉ ከቤት ካስወጣ በኋላ፣ የብላቴናዪቱን አባትና እናት እንዲሁም ዐብረውት የመጡትን ደቀ መዛሙርት አስከትሎ ብላቴናዪቱ ወዳለችበት ገባ። ከዚያም የብላቴናዪቱን እጅ ይዞ፣ “ጣሊታ ቁሚ!” አላት፤ ትርጕሙም፣ “አንቺ ልጅ ተነሺ” ማለት ነው። ብላቴናዪቱም ወዲያውኑ ተነሥታ ቆመች፤ ወዲያ ወዲህም ሄደች። ዕድሜዋም ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር። ሰዎቹም በሁኔታው እጅግ ተደነቁ። እርሱም ይህን ነገር ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ የሚበላ ነገር እንዲሰጧትም ነገራቸው።
ማርቆስ 5 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 5
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 5:1-43
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች