ማርቆስ 3:7-19

ማርቆስ 3:7-19 NASV

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ባሕሩ ሄደ፤ ከገሊላ የመጣ እጅግ ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ የሚሠራውን ነገር የሰሙ ሰዎችም ከይሁዳ፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከኤዶምያስ፣ በዮርዳኖስ ማዶ ካለው አገር እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ ወደ እርሱ መጡ። የተሰበሰበውም ሕዝብ እንዳያጨናንቀው አነስተኛ የሆነ ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ብዙዎችን ፈውሶ ስለ ነበር፣ በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ ሊዳስሱት ይሽቀዳደሙ ነበር። ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ቍጥር ከፊቱ እየወደቁ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት ይጮኹ ነበር። እርሱ ግን ማንነቱን እንዳይገልጹ አጥብቆ ይገሥጻቸው ነበር። ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ወደ እርሱ እንዲመጡ ጠራቸው፤ እነርሱም ወደ እርሱ መጡ። ከርሱ ጋራ እንዲሆኑ፣ ለስብከትም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን ሾማቸው፤ ሐዋርያትም ብሎ ጠራቸው፤ አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። የሾማቸውም ዐሥራ ሁለቱ እነዚህ ናቸው፤ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖን፣ ቦአኔርጌስ ይኸውም፣ “የነጐድጓድ ልጆች” ብሎ የጠራው የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፤ እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ታዴዎስ፣ ቀነናዊው ስምዖን፣ እንዲሁም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች