የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 3:1-30

ማርቆስ 3:1-30 NASV

በሌላ ጊዜ ወደ ምኵራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር። በምክንያት ሊከስሱት የሚፈልጉ ሰዎችም በሰንበት ቀን ይፈውሰው እንደ ሆነ ለማየት ይጠባበቁ ነበር። እርሱም እጁ የሰለለችበትን ሰው፣ “ተነሥተህ መካከል ላይ ቁም” አለው። ኢየሱስም፣ “በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ሕይወት ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። እነርሱ ግን ዝም አሉ። በልባቸው ደንዳናነት ዐዝኖ በዙሪያው የቆሙትን በቍጣ ተመለከታቸውና ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ!” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እጁም ፍጹም ደኅና ሆነችለት። ፈሪሳውያንም እንዴት እንደሚገድሉት ከሄሮድስ ወገን ከሆኑት ጋራ መመካከር ጀመሩ። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ባሕሩ ሄደ፤ ከገሊላ የመጣ እጅግ ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ የሚሠራውን ነገር የሰሙ ሰዎችም ከይሁዳ፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከኤዶምያስ፣ በዮርዳኖስ ማዶ ካለው አገር እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ ወደ እርሱ መጡ። የተሰበሰበውም ሕዝብ እንዳያጨናንቀው አነስተኛ የሆነ ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ብዙዎችን ፈውሶ ስለ ነበር፣ በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ ሊዳስሱት ይሽቀዳደሙ ነበር። ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ቍጥር ከፊቱ እየወደቁ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት ይጮኹ ነበር። እርሱ ግን ማንነቱን እንዳይገልጹ አጥብቆ ይገሥጻቸው ነበር። ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ወደ እርሱ እንዲመጡ ጠራቸው፤ እነርሱም ወደ እርሱ መጡ። ከርሱ ጋራ እንዲሆኑ፣ ለስብከትም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን ሾማቸው፤ ሐዋርያትም ብሎ ጠራቸው፤ አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። የሾማቸውም ዐሥራ ሁለቱ እነዚህ ናቸው፤ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖን፣ ቦአኔርጌስ ይኸውም፣ “የነጐድጓድ ልጆች” ብሎ የጠራው የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፤ እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ታዴዎስ፣ ቀነናዊው ስምዖን፣ እንዲሁም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። ከዚያም ኢየሱስ ወደ አንድ ቤት ገባ፤ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ምግብ መብላት እንኳ እስኪሳናቸው ድረስ ሕዝቡ እንደ ገና በብዛት ተሰበሰበ። ሁኔታውን የሰሙ ዘመዶቹም፣ “አእምሮውን ስቷል” በማለት ይዘውት ለመሄድ ወዳለበት መጡ። ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍትም፣ “ብዔልዜቡል ዐድሮበታል! አጋንንትን የሚያወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” አሉ። እርሱም ጠራቸውና በምሳሌ እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን ሰይጣንን እንዴት ሊያስወጣ ይችላል? እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሊጸና አይችልም፤ ቤትም እርስ በርሱ ከተከፋፈለ ሊቆም አይችልም። እንደዚሁም ሰይጣን እርስ በርሱ የሚፃረርና የሚከፋፈል ከሆነ ሊቆም አይችልም፤ ያበቃለታል። ከዚህም የተነሣ አንድ ሰው አስቀድሞ ኀይለኛውን ሰው ሳያስር ወደ ኀይለኛው ሰው ቤት ሊገባና ንብረቱን ሊዘርፍ አይችልም፤ ቤቱን መዝረፍ የሚቻለው ኀይለኛውን ሰው ሲያስር ብቻ ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጆች ኀጢአትና የሚሳደቡት ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ የዘላለም ኀጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም።” ይህንም ያለው፣ “ርኩስ መንፈስ አለበት” ስላሉት ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች