የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 15:21-47

ማርቆስ 15:21-47 NASV

የአሌክሳንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን እንዲሸከም አስገደዱት። ከዚያም ኢየሱስን፣ ትርጕሙ “የራስ ቅል ስፍራ” ወደ ተባለ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት። ከከርቤ ጋራ የተቀላቀለ የወይን ጠጅም ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። ከዚያም ሰቀሉት፤ እያንዳንዱም ምን እንደሚደርሰው ለማወቅ ዕጣ ተጣጥለው ልብሱን ተከፋፈሉ። ሲሰቅሉትም ጊዜው ከጧቱ ሦስት ሰዓት ነበረ። የክሱ ጽሑፍም፣ የአይሁድ ንጉሥ የሚል ነበር። ከርሱም ጋራ ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው ሰቀሉ። [መጽሐፍ፣ “ከዐመፀኞች ጋራ ተቈጠረ” ያለውም በዚሁ ተፈጸመ።] በመንገድ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ ይሉት ነበር፤ “አዪ፤ አንተ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ፤ እስኪ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን!” እንዲሁም የካህናት አለቆችና ጸሐፍት በማሾፍ እርስ በርሳቸው እንዲህ አሉ፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም! አይተን እናምን ዘንድ ይህ ክርስቶስ፣ ይህ የእስራኤል ንጉሥ እስኪ ከመስቀል ይውረድ።” ከርሱ ጋራ የተሰቀሉትም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝም ሰዓት ኢየሱስ፣ “ኤሎሄ፣ ኤሎሄ፣ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን ይጣራል” አሉ። ከዚያም አንድ ሰው ፈጥኖ ሄዶ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ በሰፍነግ ነከረ፤ በዘንግም ሰክቶ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት፤ ከዚያም፣ “ተዉት፤ እስኪ ኤልያስ መጥቶ ሲያወርደው እናያለን” አለ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። በኢየሱስ ትይዩ ቆሞ የነበረውም የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን ሲሰጥ ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” አለ። በዚህ ጊዜ ሴቶች ከሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፣ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም፣ እንዲሁም ሰሎሜ ነበሩ፤ እነዚህ ሴቶች በገሊላ ሲከተሉትና ሲያገለግሉት የነበሩ ናቸው፤ ደግሞም ዐብረውት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሌሎች ብዙ ሴቶች ነበሩ። ጊዜው እየመሸ መጥቶ የሰንበት ዋዜማ ይኸውም የመዘጋጀት ቀን ሆነ፤ የተከበረ የሸንጎ አባልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ በድፍረት ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። ጲላጦስም እንዲህ በቶሎ መሞቱን ሲሰማ ተደነቀ፤ የመቶ አለቃውንም ወደ ራሱ ጠርቶ ከሞተ ምን ያህል ጊዜ እንደ ሆነ ጠየቀው፤ መሞቱንም ከመቶ አለቃው ካረጋገጠ በኋላ ሥጋውን ለዮሴፍ ሰጠው። ዮሴፍም በፍታ ገዛ፤ ሥጋውንም አውርዶ በበፍታው ከከፈነው በኋላ፣ ከዐለት በተወቀረ መቃብር አኖረው፤ የመቃብሩንም ደጃፍ በድንጋይ ገጠመው። ማርያም መግደላዊትና የዮሳ እናት ማርያም የት እንዳኖሩት ይመለከቱ ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች