ማርቆስ 15:21-32

ማርቆስ 15:21-32 NASV

የአሌክሳንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን እንዲሸከም አስገደዱት። ከዚያም ኢየሱስን፣ ትርጕሙ “የራስ ቅል ስፍራ” ወደ ተባለ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት። ከከርቤ ጋራ የተቀላቀለ የወይን ጠጅም ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። ከዚያም ሰቀሉት፤ እያንዳንዱም ምን እንደሚደርሰው ለማወቅ ዕጣ ተጣጥለው ልብሱን ተከፋፈሉ። ሲሰቅሉትም ጊዜው ከጧቱ ሦስት ሰዓት ነበረ። የክሱ ጽሑፍም፣ የአይሁድ ንጉሥ የሚል ነበር። ከርሱም ጋራ ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው ሰቀሉ። [መጽሐፍ፣ “ከዐመፀኞች ጋራ ተቈጠረ” ያለውም በዚሁ ተፈጸመ።] በመንገድ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ ይሉት ነበር፤ “አዪ፤ አንተ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ፤ እስኪ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን!” እንዲሁም የካህናት አለቆችና ጸሐፍት በማሾፍ እርስ በርሳቸው እንዲህ አሉ፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም! አይተን እናምን ዘንድ ይህ ክርስቶስ፣ ይህ የእስራኤል ንጉሥ እስኪ ከመስቀል ይውረድ።” ከርሱ ጋራ የተሰቀሉትም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች