“ ‘የጥፋት ርኩሰት’ ስፍራው ባልሆነ ቦታ ቆሞ በምታዩት ጊዜ አንባቢው ያስተውል፤ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በቤቱ ጣራ ላይ ያለ አይውረድ፤ ንብረቱንም ለማውጣት ወደ ቤቱ አይግባ፤ በዕርሻ ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ። በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! ይህም በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በእነዚያ ቀናት፣ እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ እስከ አሁን ድረስ፣ ከዚህም በኋላ ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል። “ጌታ ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ማንም ሥጋ ለባሽ ባልዳነ ነበር፤ ስለ መረጣቸው ስለ ምርጦቹ ሲል ግን ቀኖቹን አሳጥሯል። በዚያ ጊዜ ማንም፣ ‘እነሆ፤ ክርስቶስ እዚህ ነው!’ ቢላችሁ ወይም፣ ‘እነሆ፤ እዚያ ነው!’ ቢላችሁ አትመኑ። ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ተነሥተው፣ ምልክቶችንና ድንቆችን በማድረግ፣ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ያስታሉ። ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ጊዜው ሳይደርስ ሁሉን ነግሬአችኋለሁ። “በዚያ ጊዜ፣ ከመከራው በኋላ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፣ “ ‘ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናወጣሉ።’ “በዚያ ጊዜም የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ግርማ በደመና ሲመጣ ያዩታል። እርሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማያት ዳርቻ ምርጦቹን ይሰበስባል። “ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ እንደ ቀረበ፣ በደጅም እንደ ሆነ ዕወቁ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች እስከሚፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፤ ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም። “ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ከአብ በቀር፣ የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም። ስለዚህ ጊዜው መቼ እንደሚሆን ስለማታውቁ ተጠንቀቁ! ትጉ! ጸልዩም! ይህም ቤቱን ለባሮቹ ትቶ፣ እያንዳንዱን አገልጋይ በየሥራ ድርሻው ላይ አሰማርቶ፣ በረኛው ነቅቶ እንዲጠብቅ አዝዞ የሄደውን ሰው ይመስላል። “እንግዲህ የቤቱ ባለቤት በምሽት ወይም በውድቅት፣ በዶሮ ጩኸት ወይም ጎሕ ሲቀድድ እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ፤ ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ፤ ለእናንተ የምነግራችሁን ለሰው ሁሉ እናገራለሁ፤ ‘ተግታችሁ ጠብቁ!’ ”
ማርቆስ 13 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 13
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 13:14-37
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች