ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማቸው፤ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠቱን አስተውሎ፣ “ለመሆኑ ከትእዛዞች ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን፣ ጌታ አንድ ነው። አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’ ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።’ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።” ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እግዚአብሔር አንድ መሆኑን፣ ከርሱም ሌላ አለመኖሩን እውነት ተናግረሃል፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።” ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፣ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ “ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ? ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፣ “ ‘ጌታ ጌታዬን፣ “ጠላቶችህን ከእግሮችህ በታች እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው። ይላል፤’ ታዲያ ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ካለው፣ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰማው ነበር። ሲያስተምርም እንዲህ አለ፤ ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ “ዘርፋፋ ቀሚስ ለብሰው መዞርን፣ በገበያ ስፍራ የአክብሮት ሰላምታን፣ በምኵራብ የከበሬታ መቀመጫን፣ በግብዣ ቦታም የክብር ስፍራን ይፈልጋሉና፤ በረዥም ጸሎታቸው እያሳበቡ የመበለቶችን ቤት ያራቍታሉ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።” ኢየሱስ በመባ መክተቻው ሣጥን ትይዩ ተቀምጦ፣ ብዙ ሰዎች ስጦታቸውን ሲያስገቡ ይመለከት ነበር። ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ አስገቡ፤ አንዲት ምስኪን መበለት ግን ከአንድ ሳንቲም የማይበልጡ ሁለት የናስ ሳንቲሞች አስገባች። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት ሙዳየ መባ ውስጥ ሌሎቹ ከጨመሩት የበለጠ አስገባች። እነዚህ ሁሉ ከተረፈው ሀብታቸው ሰጡ፤ እርሷ ግን ከጕድለቷ ያላትን፣ መኖሪያዋን ሁሉ ሰጠች።”
ማርቆስ 12 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 12
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 12:28-44
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos