ዮሐንስ እስር ቤት ከገባ በኋላ፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ ሄዶ፣ “ጊዜው ደርሷል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ!” እያለ ይሰብክ ነበር። ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፣ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ፣ መረብ ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው። ኢየሱስም፣ “ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ትንሽ ዕልፍ እንዳለ፣ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን በጀልባ ሆነው መረባቸውን ሲያበጃጁ አያቸውና፣ ወዲያውኑ ጠራቸው። እነርሱም አባታቸውን በጀልባው ላይ ከቅጥር ሠራተኞቹ ጋራ ትተው ተከተሉት። ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ፤ ኢየሱስም ወዲያው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። እንደ ጸሐፍት ሳይሆን፣ እንደ ባለሥልጣን በማስተማሩ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ። በዚያ ጊዜ በምኵራባቸው ውስጥ የነበረ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው እንዲህ በማለት ጮኸ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኛ ምን ትሻለህ? ልታጠፋን መጣህን? እኔ ማን እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” ኢየሱስም፣ “ጸጥ በል፤ ከርሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን በኀይል ካንፈራገጠው በኋላ እየጮኸ ከርሱ ወጣ። ሁሉም በመገረም፣ “ይህ ሥልጣን ያለው አዲስ ትምህርት ምንድን ነው? ርኩሳን መናፍስትን እንኳ ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል!” እያሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ። ወዲያውም ዝናው በገሊላ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች ሁሉ ወጣ። ወዲያው ከምኵራብ እንደ ወጡ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋራ ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገቡ። የስምዖን ዐማት በትኵሳት በሽታ ታምማ ተኝታ ነበር፤ ስለ እርሷም ነገሩት፤ ስለዚህም እርሱ ወደ ተኛችበት በመሄድ እጇን ይዞ አስነሣት፤ ትኵሳቱም ተዋት፤ ተነሥታም ታገለግላቸው ጀመር። ጀንበር ከጠለቀች በኋላ፣ ምሽት ላይ የአካባቢው ሰዎች ሕመምተኞችንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ። የከተማዋ ሕዝብ በሙሉ በቤቱ ደጅ ላይ ተሰብስቦ ነበር። እርሱም በተለያየ በሽታ የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፤ ብዙ አጋንንትም አወጣ፤ ነገር ግን አጋንንቱ የኢየሱስን ማንነት ያውቁ ስለ ነበር እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም። ማለዳም ገና ጎሕ ሳይቀድድ፣ ኢየሱስ ተነሥቶ ከቤት ወጣ፤ ወደ ምድረ በዳም ሄዶ ይጸልይ ጀመር። ስምዖንና ባልደረቦቹም ተከትለው ይፈልጉት ነበር፤ ባገኙትም ጊዜ፣ “ሰው ሁሉ ይፈልግሃል!” አሉት። እርሱም፣ “ከዚህ ተነሥተን በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ፤ እዚያም ልስበክ፤ የመጣሁት ለዚሁ ነውና” አላቸው። ስለዚህ በምኵራቦቻቸው እየሰበከና አጋንንትን በማስወጣት በመላዋ ገሊላ ይዘዋወር ጀመር። አንድ ለምጻም ወደ እርሱ ቀርቦ ከፊቱ በመንበርከክ፣ “ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ለመነው። ኢየሱስም ለሰውየው በመራራት እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “እፈቅዳለሁ፣ ንጻ!” አለው። እርሱም ወዲያው ከለምጹ ነጻ፤ ከበሽታውም ተፈወሰ። ኢየሱስም ሰውየውን አጥብቆ በማስጠንቀቅ እንዲህ ሲል አሰናበተው፤ “ለማንም አንድ ነገር እንኳ እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ምስክር እንዲሆናቸው ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ስለ መንጻትህም ሙሴ ያዘዘውን መሥዋዕት አቅርብ” አለው። ሰውየው ግን በሄደበት ሁሉ ነገሩን በሰፊው አወራ፤ ወሬውንም አሠራጨ። በዚህ ምክንያት ኢየሱስ ወደ ማንኛውም ከተማ በግልጽ መግባት አልተቻለውም፤ ከዚህም የተነሣ ከከተማ ውጭ በሚገኙ ምድረ በዳዎች መኖር ጀመረ፤ ሰዎች ግን ከየአቅጣጫው እርሱ ወዳለበት መምጣት አላቋረጡም።
ማርቆስ 1 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 1
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 1:14-45
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos