የእግዚአብሔር ልጅ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ። በነቢዩ በኢሳይያስ፣ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ “እነሆ፤ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፤” “የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ‘ጥርጊያውንም አስተካክሉ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ድምፅ።” ስለዚህ መጥምቁ ዮሐንስ በበረሓ እያጠመቀና ለኀጢአት ስርየት የንስሓ ጥምቀት እየሰበከ መጣ። በመላው ይሁዳ፣ የኢየሩሳሌም ሰዎችም በጠቅላላ ወደ እርሱ በመሄድ ኀጢአታቸውን እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በርሱ እጅ ተጠመቁ። ዮሐንስ የግመል ጠጕር ይለብስ፣ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ፣ አንበጣና የበረሓ ማርም ይበላ ነበር። ስብከቱም፣ “እኔ ጐንበስ ብዬ የጫማውን ማሰሪያ መፍታት ከማይገባኝ፣ ከእኔ የሚበረታው ከእኔ በኋላ ይመጣል። እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል” የሚል ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የገሊላ ከተማ ከሆነችው ከናዝሬት መጥቶ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። ከውሃው በሚወጣበትም ጊዜ፣ ሰማያት ተከፍተው፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ በርሱ ላይ ሲወርድ አየ፤ “የምወድድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። ወዲያውም መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድረ በዳ መራው፤ በሰይጣንም እየተፈተነ አርባ ቀን በምድረ በዳ ቈየ። ከአራዊት ጋራ ነበር፤ መላእክትም አገለገሉት። ዮሐንስ እስር ቤት ከገባ በኋላ፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ ሄዶ፣ “ጊዜው ደርሷል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ!” እያለ ይሰብክ ነበር። ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፣ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ፣ መረብ ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው። ኢየሱስም፣ “ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ትንሽ ዕልፍ እንዳለ፣ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን በጀልባ ሆነው መረባቸውን ሲያበጃጁ አያቸውና፣ ወዲያውኑ ጠራቸው። እነርሱም አባታቸውን በጀልባው ላይ ከቅጥር ሠራተኞቹ ጋራ ትተው ተከተሉት። ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ፤ ኢየሱስም ወዲያው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። እንደ ጸሐፍት ሳይሆን፣ እንደ ባለሥልጣን በማስተማሩ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ። በዚያ ጊዜ በምኵራባቸው ውስጥ የነበረ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው እንዲህ በማለት ጮኸ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኛ ምን ትሻለህ? ልታጠፋን መጣህን? እኔ ማን እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” ኢየሱስም፣ “ጸጥ በል፤ ከርሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን በኀይል ካንፈራገጠው በኋላ እየጮኸ ከርሱ ወጣ። ሁሉም በመገረም፣ “ይህ ሥልጣን ያለው አዲስ ትምህርት ምንድን ነው? ርኩሳን መናፍስትን እንኳ ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል!” እያሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ። ወዲያውም ዝናው በገሊላ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች ሁሉ ወጣ።
ማርቆስ 1 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 1
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 1:1-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos