የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 8

8
የለምጻሙ መንጻት
8፥2-4 ተጓ ምብ – ማር 1፥40-44ሉቃ 5፥12-14
1ከተራራው በወረደ ጊዜም ብዙ ሕዝብ ተከተለው። 2እነሆ፤ አንድ ለምጻም#8፥2 የግሪኩ ቃል የግድ ከለምጽ ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን፣ የተለያዩ የቈዳ በሽታዎችንም ያመለክታል። ሰው ወደ ኢየሱስ ቀረበና ከፊቱ ተንበርክኮ እየሰገደለት፣ “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው።
3ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “ፈቃዴ ነው፤ ንጻ!” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። 4ከዚያም ኢየሱስ፣ “መፈወስህን ለማንም አታውራ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ፤ ይህም ምስክር ይሆንላቸዋል” አለው።
የመቶ አለቃው እምነት
8፥5-13 ተጓ ምብ – ሉቃ 7፥1-10
5ኢየሱስ ቅፍርናሆም እንደ ደረሰ አንድ የመቶ አለቃ ቀርቦ፣ እንዲህ ሲል ለመነው፤ 6“ጌታ ሆይ፤ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ እጅግ በመሠቃየት ከቤት ተኝቷል” አለው።
7ኢየሱስም፣ “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው።
8የመቶ አለቃው ግን መልሶ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ቤቴ እንድትገባ የሚገባኝ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከዚሁ ሆነህ አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ አገልጋዬም ይፈወሳል፤ 9እኔ ራሴ የምታዘዛቸው አለቆች፣ ለእኔም የሚታዘዙ የበታቾች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን፣ ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።”
10ኢየሱስም በመልሱ ተደንቆ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእስራኤል መካከል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው አንድ ሰው አላገኘሁም፤ 11እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማይ ማእድ ዙሪያ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ይቀመጣሉ፤ 12መንግሥተ ሰማይ ተዘጋጅቶላቸው የነበሩት ግን ወደ ውጭ ወደ ጨለማው ይጣላሉ። በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”
13ኢየሱስም መቶ አለቃውን፣ “ሂድ! እንደ እምነትህ ይሁንልህ” አለው። አገልጋዩም በዚያች ቅጽበት ተፈወሰ።
ኢየሱስ ብዙዎችን መፈወሱ
8፥14-16 ተጓ ምብ – ማር 1፥29-34ሉቃ 4፥38-41
14ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት ጐራ ሲል የጴጥሮስ ዐማት በትኵሳት ታምማ ተኝታ አገኛት። 15እጇን ዳሰሳት፤ ትኵሳቱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለችው።
16በዚያ ምሽት በአጋንንት የተያዙ ብዙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም መናፍስትን በቃሉ አስወጣ፤ በሽተኞችንም ሁሉ ፈወሰ። 17በዚህም ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ፤
“እርሱ ደዌያችንን ተቀበለ፤
ሕመማችንንም ተሸከመ።”
የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን ውሳኔ ይጠይቃል
8፥19-22 ተጓ ምብ – ሉቃ 9፥57-60
18ኢየሱስ ብዙ ሰዎች በዙሪያው ተሰብስበው ባየ ጊዜ፣ ወደ ባሕሩ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዛቸው። 19በዚህ ጊዜ አንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህር ወደ እርሱ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፤ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።
20ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጐጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት ቦታ የለውም” ሲል መለሰለት።
21ደቀ መዝሙር የሆነ አንድ ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው።
22ኢየሱስ ግን፣ “ሙታን ሙታናቸውን ይቅበሩ፤ አንተ ተከተለኝ” አለው።
ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ
8፥23-27 ተጓ ምብ – ማር 4፥36-41ሉቃ 8፥22-25
8፥23-27 ተጓ ምብ – ማቴ 14፥22-23
23ከዚያም ኢየሱስ ወደ ጀልባ ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከትለውት ገብተው ሄዱ። 24ድንገት ኀይለኛ ማዕበል በባሕሩ ላይ ተነሥቶ ጀልባዪቱን እስኪሸፍን ድረስ አወካቸው፤ በዚህ ጊዜ ግን ኢየሱስ ተኝቶ ነበር። 25ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው ቀሰቀሱትና፣ “ጌታ ሆይ! ጠፋን፤ አድነን” አሉት።
26ኢየሱስም፣ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ ለምን ይህን ያህል ፈራችሁ?” አላቸው፤ ከዚያም ተነሥቶ ነፋሱንና ማዕበሉን ገሠጸ፤ ወዲያውም ጸጥታ ሰፈነ።
27ሰዎቹም፣ “ነፋስና ባሕር እንኳ የሚታዘዙለት፣ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው?” እያሉ ተደነቁ።
ከርኩሳን መናፍስት ስለ ተፈወሱ ሁለት ሰዎች
8፥28-34 ተጓ ምብ – ማር 5፥1-17ሉቃ 8፥26-27
28ባሕሩን ተሻግሮ ጌርጌሴኖን#8፥28 አንዳንድ ቅጆች ጌራሴኖን ይላሉ። ወደሚባል አገር እንደ ደረሰ፣ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከሚኖሩበት የመቃብር ቦታ ወጥተው ተገናኙት። በዚያ መንገድ ሰው ማለፍ እስከማይችል ድረስ እጅግ አደገኞች ነበሩ። 29እነርሱም “የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፤ ከእኛ ምን ጕዳይ አለህ? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን መጣህን?” እያሉ ጮኹ።
30ከእነርሱ ትንሽ ራቅ ብሎ፣ የብዙ ዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር። 31አጋንንቱም ኢየሱስን፣ “የምታስወጣን ከሆነ ዐሣማዎቹ መንጋ ውስጥ እንድንገባ ፍቀድልን” ብለው ለመኑት።
32ኢየሱስም፣ “ሂዱ!” አላቸው። አጋንንቱም ከሰዎቹ ወጥተው ዐሣማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ ዐሣማዎቹም በሙሉ ከነበሩበት አፋፍ እየተጣደፉ ባሕሩ ውስጥ በመግባት ውሃው ውስጥ ሰጥመው ሞቱ። 33የዐሣማዎቹ ጠባቂዎችም ሸሽተው ወደ ከተማ በመሄድ፣ የሆነውን ሁሉና በአጋንንት ተይዘው በነበሩት ሰዎች ላይ የተደረገውን ነገር አወሩ። 34እነሆም፤ መላው የከተማ ነዋሪ ኢየሱስን ለመገናኘት ወጣ፤ ባዩትም ጊዜ አገራቸውን ለቅቆ እንዲሄድ ለመኑት።

Currently Selected:

ማቴዎስ 8: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ