የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 3:1-17

ማቴዎስ 3:1-17 NASV

በዚያን ወራት መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። ስብከቱም፣ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” የሚል ነበር። በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረለት እርሱ ነው፤ “በምድረ በዳ፣ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጐዳናውንም አስተካክሉ’ እያለ የሚጮኽ ድምፅ።” የዮሐንስ ልብስ የግመል ጠጕር ሲሆን፣ ወገቡንም በጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሓ ማር ነበር። ከኢየሩሳሌም፣ ከመላው ይሁዳና በዮርዳኖስ ዙሪያ ካለው አገር ሁሉ ሰዎች ወደ ዮሐንስ ይጐርፉ፣ ኀጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በእርሱ እጅ ይጠመቁ ነበር። ብዙ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደሚያጠምቅበት ስፍራ ሲመጡ ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “እናንት የእፉኝት ልጆች! ለመሆኑ ከሚመጣው ቍጣ እንድታመልጡ ማን መከራችሁ? ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ ‘አብርሃም አባት አለን’ በማለት ራሳችሁን አታታልሉ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣ ይችላል እላችኋለሁና። እነሆ፤ ምሣር የዛፎችን ሥር ሊቈርጥ ተዘጋጅቷል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል። “እኔ ለንስሓ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ጫማውን መሸከም የማይገባኝ፣ ከእኔ የሚበልጥ ኀያል ከእኔ በኋላ ይመጣል። እርሱም በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል። መንሹ በእጁ ነው፤ ዐውድማውን ያጠራል፤ ስንዴውን በጐተራ ይከትታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። ዮሐንስ ግን፣ “ይህማ አይሆንም፤ እኔ ባንተ መጠመቅ ሲያስፈልገኝ እንዴት አንተ ወደ እኔ ትመጣለህ?” ብሎ ተከላከለ። ኢየሱስም፣ “ግድ የለም ፍቀድልኝ፤ ይህን በማድረግ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” አለው፤ ዮሐንስም በነገሩ ተስማማ። ኢየሱስም እንደ ተጠመቀ ከውሃው ወጣ፤ ወዲያውኑም ሰማይ ተከፍቶ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድበት አየ። እነሆ፤ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}