የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 28:1-8

ማቴዎስ 28:1-8 NASV

ሰንበት ካለፈ በኋላ፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ጎሕ ሲቀድድ፣ ማርያም መግደላዊትና ሌላዋ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ ሄዱ። በድንገት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የጌታም መልአክ ከሰማይ ወርዶ ወደ መቃብሩ በመሄድ ድንጋዩን አንከባልሎ በላዩ ላይ ተቀመጠበት፤ መልኩ እንደ መብረቅ ብሩህ፣ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበር። ጠባቂዎቹ መልአኩን ከመፍራት የተነሣ ተንቀጠቀጡ፤ እንደ በድንም ሆኑ። መልአኩም ሴቶቹን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ ዐውቃለሁና፤ እርሱ በዚህ የለም፤ እንደ ተናገረው ተነሥቷል፤ ኑና ተኝቶበት የነበረውን ቦታ እዩ። አሁንም ፈጥናችሁ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ፣ ‘ከሙታን ተነሥቷል፤ ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ በዚያ ታዩታላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው። እንግዲህ ነግሬአችኋለሁ!” ሴቶቹም በፍርሀትና በደስታ ተሞልተው ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር በፍጥነት እየሮጡ የመቃብሩን ስፍራ ትተው ሄዱ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች