ማቴዎስ 27:32-52

ማቴዎስ 27:32-52 NASV

ይዘውትም ሲሄዱ ስምዖን ተብሎ የሚጠራ የቀሬና ሰው አገኙ፤ መስቀሉንም እንዲሸከም አስገደዱት። ትርጕሙ፣ “የራስ ቅል ስፍራ” ከሆነው ጎልጎታ ከተባለው ቦታ ሲደርሱ፣ ከሐሞት ጋራ የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን ቀምሶ ሊጠጣው አልፈቀደም። ከሰቀሉትም በኋላ ዕጣ ጥለው ልብሱን ተካፈሉ፤ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። ከራስጌውም፣ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው” የሚል የክስ ጽሑፍ አኖሩ። ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኙ፣ አንዱ በግራው ዐብረውት ተሰቅለው ነበር። በመንገድ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ ይሉት ነበር፤ “አንተ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ፤ እስኪ ራስህን አድን! የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ!” ይሉት ነበር። የካህናት አለቆችም ከኦሪት ሕግ መምህራንና ከሽማግሌዎች ጋራ ሆነው እያሾፉበት እንዲህ ይሉ ነበር፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እናምንበታለን። በእግዚአብሔር ታምኗል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ይል ስለ ነበር እስኪ ከወደደው አሁን ያድነው!” ከርሱ ጋራ የተሰቀሉት ወንበዴዎችም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር። ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓት ገደማ፣ ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” እያለ ጮኸ፤ ትርጕሙም “አምላኬ፤ አምላኬ፤ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ጩኸቱን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን እየተጣራ ነው!” አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጦ ሰፍነግ በመውሰድ የኮመጠጠ ወይን ጠጅ ውስጥ ነከረው፤ ሰፍነጉንም በሸንበቆ ዘንግ ጫፍ ላይ በማድረግ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት። የቀሩት ግን፣ “ተዉት፤ እስኪ ኤልያስ መጥቶ ሲያድነው እናያለን!” አሉ። ኢየሱስ እንደ ገና ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ፤ መንፈሱንም አሳልፎ ሰጠ። በዚያ ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፤ ምድር ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጣጠቁ፤ መቃብሮች ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው የነበሩትም ብዙዎች ቅዱሳን ተነሡ፤

ተዛማጅ ቪዲዮዎች