በመናገር ላይ እያለ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ዘንድ የተላኩ ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎችም ዐብረውት ነበሩ። ይሁዳም፣ “እኔ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ ምልክት ሰጥቷቸው ስለ ነበር፣ በቀጥታ ወደ ኢየሱስ ሄዶ፣ “መምህር ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት ሳመው። ኢየሱስም፣ “ወዳጄ ሆይ፤ የመጣህበትን ፈጽም” አለው። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ቀርበው ኢየሱስን ያዙት፤ አሰሩትም። ከኢየሱስ ጋራ ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ። ካስፈለገ አባቴን ብለምነው ከዐሥራ ሁለት ክፍለ ሰራዊት የሚበልጡ መላእክት የማይሰድድልኝ ይመስልሃል? ይህ ቢሆን ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት ይሆናል ያሉት ነገር እንዴት ይፈጸማል?” በዚያ ጊዜ ኢየሱስ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “ወንበዴ እንደሚይዝ ሰው ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁ? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ተቀምጬ ሳስተምር አልያዛችሁኝም ነበር፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው ነቢያት በቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩት ይፈጸም ዘንድ ነው።” በዚያ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ጥለውት ሸሹ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፣ የኦሪት የሕግ መምህራንና የሕዝብ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ነበሩበት፣ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ነገር ግን ጴጥሮስ ከርቀት ሆኖ እስከ ሊቀ ካህናቱ ቅጥር ግቢ ይከተለው ነበር፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የሁኔታውን መጨረሻ ለማየት ከጠባቂዎቹ ጋራ ተቀመጠ። በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ በሙሉ ኢየሱስን ለማስገደል የሐሰት ማስረጃ ይፈልጉ ነበር፤ ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢቀርቡም በቂ ማስረጃ አላገኙም። በኋላ ግን ሁለት ሰዎች ቀርበው፣ “ይህ ሰው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ውስጥ መልሼ ልሠራው እችላለሁ’ ብሏል” በማለት ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ተነሥቶ በመቆም፣ “እነዚህ ሰዎች ለሚመሰክሩብህ ሁሉ ምንም መልስ አትሰጥምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም፣ “በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ ንገረን” አለው።
ማቴዎስ 26 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 26
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 26:47-63
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች