“ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ። እንደዚሁም እነዚህን ሁሉ ስታዩ፣ እርሱ በደጅ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም። “ነገር ግን ስለዚያች ቀንና ሰዓት ከአብ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም። ልክ በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል፤ ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከቡ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስም ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ ድንገት የጥፋት ውሃ እንዳጥለቀለቃቸው፣ የሰው ልጅ ሲመጣም እንደዚሁ ይሆናል። በዚያ ጊዜ ሁለት ሰዎች በዕርሻ ላይ ይውላሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፣ ሌላዋ ትቀራለች። “እንግዲህ ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ። ይህን ልብ በሉ፤ ባለቤቱ ሌሊት ሌባ በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ፣ ቤቱም እንዳይደፈር በተጠባበቀ ነበር። ስለዚህ የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣል፤ እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ። “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ባለቤቱ በቤተ ሰዎቹ ላይ የሾመው ታማኝና ብልኅ ባሪያ እንግዲህ ማነው? ጌታው ሲመለስ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ባሪያ እርሱ ምስጉን ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ነገር ግን ያ ባሪያ ክፉ ቢሆንና በልቡ፣ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ በማለት፣ ተነሥቶ ሌሎች አገልጋይ ባልንጀሮቹን መምታት ቢጀምር፣ ከሰካራሞችም ጋራ ቢበላና ቢጠጣ፣ ባሪያው ባልጠበቀው ቀንና ባላሰበው ሰዓት ጌታው መጥቶ፣ ይቈራርጠዋል፤ ዕድል ፈንታውንም ከግብዞች ጋራ ያደርግበታል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
ማቴዎስ 24 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 24
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 24:32-51
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos