ከዚያም ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ላይ ተቀምጠዋል። ስለዚህ የሚነግሯችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ነገር ግን እንደሚናገሩት አያደርጉምና ተግባራቸውን አትከተሉ። እንዲሁም ለመሸከም የማይቻል ከባድ ሸክም አስረው በሰዎች ትከሻ ላይ ይጭናሉ፤ ራሳቸው ግን በጣታቸው እንኳ አይነኩትም። “ለመታየት ሲሉ የሚያደርጉትን ሁሉ በሰው ፊት ያደርጋሉ፤ አሸንክታባቸውን ያሰፋሉ፤ የቀሚሳቸውን ዘርፍ ያስረዝማሉ። በግብዣ ቦታ የከበሬታ ስፍራ፣ በምኵራብም የመጀመሪያውን መቀመጫ መያዝ ይወድዳሉ። እንዲሁም በገበያ መካከል ሰላምታ መቀበልንና በሰዎች አንደበት ‘መምህር’ ተብለው መጠራትን ይሻሉ። “እናንተ ግን ‘መምህር’ ተብላችሁ አትጠሩ፤ አስተማሪያችሁ አንድ ብቻ ነው፤ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁና። በሰማይ ያለ አንድ አባት ስላላችሁ፣ በምድር ማንንም ‘አባት’ ብላችሁ አትጥሩ። መምህራችሁ አንዱ ክርስቶስ ስለሆነ፣ ‘መምህር’ ተብላችሁ አትጠሩ። ከመካከላችሁ ከሁላችሁ የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል፤ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ይዋረዳል፣ ራሱን የሚያዋርድ ግን ይከበራል። “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማይ እንዳይገቡ በሰዎች ላይ በሩን ስለምትዘጉባቸው ወዮላችሁ! እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ መግባት የሚፈልጉትንም አታስገቡም። እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ የመበለቶችን ቤት እያራቈታችሁ፣ ለሰው ይምሰል ረዥም ጸሎት ስለምታደርጉ የከፋ ፍርድ ትቀበላላችሁ። “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ አንድን ሰው ወደ አይሁድ ሃይማኖት ለማስገባት በባሕርና በየብስ ስለምትጓዙ፣ ባመነም ጊዜ ከእናንተ በዕጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት ወዮላችሁ። “እናንተ ዕውር መሪዎች፤ ወዮላችሁ! ‘ማንም በቤተ መቅደስ ቢምል ምንም አይደለም፤ ነገር ግን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባለው ወርቅ ቢምል መሐላው ይደርስበታል’ ትላላችሁ። እናንተ የታወራችሁ ተላላዎች! ከወርቁና ወርቁን ከቀደሰው ቤተ መቅደስ የቱ ይበልጣል? እንዲሁም፣ ‘ማንም በመሠዊያው ቢምል ምንም አይደለም፤ ነገር ግን በላዩ ላይ ባለው መባ ቢምል መሐላው ይደርስበታል’ ትላላችሁ፤ እናንተ ዕውሮች፤ ከመባውና መባውን ከቀደሰው መሠዊያ የቱ ይበልጣል? ስለዚህ፣ በመሠዊያው የማለ፣ በመሠዊያውና በላዩ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል። እንዲሁም በቤተ መቅደሱ የማለ፣ በቤተ መቅደሱና በውስጡ በሚያድረው ይምላል። በሰማይ የማለም በእግዚአብሔር ዙፋንና በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ይምላል። “እናንት ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት እየሰጣችሁ በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና፤ እነዚያን ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ በተገባችሁ ነበር፤ እናንት የታወራችሁ መሪዎች፤ ትንኝን አጥርታችሁ ትጥላላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ። “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ትወለውላላችሁ፤ በውስጣቸው ግን ቅሚያና ሥሥት ሞልቶባቸዋል። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጥ አጽዳ፤ ከዚያም ውጭው የጸዳ ይሆናል። “እናንት ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ውጫቸው በኖራ ተለስነው የሚያምሩ፣ ውስጣቸው ግን በሙታን ዐፅምና በብዙ ርኩሰት የተሞላ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ! እናንተም በውጭ ለሰዎች ጻድቃን ትመስላላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በግብዝነትና በክፋት የተሞላ ነው። “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! የነቢያትን መቃብር እየገነባችሁ፣ የጻድቃንንም ሐውልት እያስጌጣችሁ፣ ‘በአባቶቻችን ዘመን ብንኖር ኖሮ፣ የነቢያትን ደም በማፍሰስ አንተባበራቸውም ነበር’ ትላላችሁና። በዚህም የነቢያት ገዳዮች ለነበሩት አባቶቻችሁ ልጆች መሆናችሁን በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ። እንግዲህ የአባቶቻችሁን ጅምር ተግባር ከፍጻሜ አድርሱ! “እናንተ እባቦች፤ የእፉኝት ልጆች! ከገሃነም ፍርድ እንዴት ልታመልጡ ትችላላችሁ? ስለዚህ ነቢያትን፣ ጠቢባንንና መምህራንን እልክላችኋለሁ፤ ከነዚህም አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ፤ አንዳንዶቹን ትሰቅላላችሁ፤ ሌሎቹንም በምኵራቦቻችሁ ትገርፏቸዋላችሁ፤ ከከተማ ወደ ከተማ ታሳድዷቸዋላችሁ። ስለዚህ፣ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በመቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ፣ በምድር ላይ ለፈሰሰው ንጹሕ ደም ሁሉ እናንተ ተጠያቂዎች ናችሁ።
ማቴዎስ 23 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 23
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 23:1-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos