በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን፣ ኢየሱስ በቤተ ልሔም ይሁዳ ከተወለደ በኋላ፣ ጠቢባን ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና” ሲሉ ጠየቁ። ንጉሡ ሄሮድስ ይህን በሰማ ጊዜ ታወከ፤ እንዲሁም መላዪቱ ኢየሩሳሌም አብራ ታወከች። እርሱም የካህናት አለቆችንና የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንን በሙሉ ሰብስቦ፣ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “በይሁዳ ቤተ ልሔም፤ ነቢዩ እንዲህ ብሎ ጽፏልና አሉ፤ “ ‘በይሁዳ ምድር የምትገኚው አንቺ ቤተ ልሔም፣ ከሌሎቹ የይሁዳ ገዦች በምንም አታንሺም፤ የሕዝቤ የእስራኤል ጠባቂ የሚሆን፣ ከአንቺ ይወጣልና።’ ” ከዚያም ሄሮድስ ጠቢባኑን በምስጢር አስጠርቶ በማነጋገር ኮከቡ የታየበትን ትክክለኛ ጊዜ ተረዳ። ጠቢባኑንም ወደ ቤተ ልሔም ልኮ፣ “ሂዱና ሕፃኑን ፈልጉ፤ እኔም ደግሞ ሄጄ እንድሰግድለት፣ እንዳገኛችሁት ወደ እኔ ተመልሳችሁ የት እንዳለ ንገሩኝ” አላቸው። ጠቢባኑ ንጉሡ ያለውን ከሰሙ በኋላ ጕዟቸውን ቀጠሉ። ይህም በምሥራቅ ያዩት ኮከብ እየመራቸው ሕፃኑ እስካለበት ድረስ ወሰዳቸው። ኮከቡንም ሲያዩ ከመጠን በላይ ተደሰቱ። ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩ፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ሣጥኖቻቸውን ከፍተው ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤም አቀረቡለት። እግዚአብሔርም ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ባስጠነቀቃቸው መሠረት፣ መንገድ አሳብረው ወደ አገራቸው ተመለሱ። ጠቢባኑ ከሄዱ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ “ተነሥ! የምትመለስበትን ጊዜ እስካስታውቅህ ድረስ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ በመሸሽ በዚያ ቈይ፤ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻልና” አለው። ስለዚህም ዮሴፍ ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብፅ ሄደ፤ በዚያም ሄሮድስ እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ኖረ። በዚህም፣ “ልጄን ከግብፅ ምድር ጠራሁት” በማለት እግዚአብሔር በነቢዩ አንደበት የተናገረው ቃል ተፈጸመ። ሄሮድስ ጠቢባኑ እንዳታለሉት በተረዳ ጊዜ በጣም ተናደደ። ከጠቢባኑ በተነገረው መሠረት፣ ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን የቤተ ልሔምንና የአካባቢዋን መንደሮች ወንድ ልጆች ሁሉ ልኮ አስገደለ። በዚህም በነቢዩ በኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤ “የልቅሶና የታላቅ ዋይታ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች፤ መጽናናትም አልቻለችም፤ ልጆቿ ሁሉ ዐልቀዋልና።”
ማቴዎስ 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 2
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 2:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos