ማቴዎስ 15
15
የፈሪሳውያን ወግ
15፥1-20 ተጓ ምብ – ማር 7፥1-23
1ከዚያም ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና የኦሪት ሕግ መምህራን ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ 2“ደቀ መዛሙርትህ የአባቶችን ወግ የሚሽሩት ለምንድን ነው? ምግብ ሲበሉኮ እጃቸውን አይታጠቡም” አሉት።
3ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እናንተስ ለወጋችሁ ስትሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትሽራላችሁ? 4እግዚአብሔር፣ ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ በአባቱ ወይም በእናቱ ላይ ክፉ ቃል የሚናገር ይገደል’ ብሎ ሲያዝዝ፣ 5እናንተ ግን፣ ማንም ሰው አባቱን ወይም እናቱን፣ ‘ላደርግላችሁ የሚገባውን ማንኛውንም ነገር ለእግዚአብሔር መባ አድርጌ አቅርቤአለሁ’ ቢላቸው፣ 6‘አንድ ሰው ይህን ካደረገ ዘንድ አባቱን ወይም እናቱን አክብሯል’ ትላላችሁ። ስለዚህ ለወጋችሁ ብላችሁ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ። 7እናንት ግብዞች፤ ኢሳይያስ ስለ እናንተ እንዲህ ብሎ በትንቢት የተናገረው ትክክል ነው፤
8 “ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤
ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤
9 በከንቱ ያመልኩኛል፣
ትምህርታቸውም የሰው ሥርዐት ነው።’ ”
10ሕዝቡን ወደ እርሱ ቀረብ እንዲሉ አድርጎ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙ፤ አስተውሉም፤ 11ሰውን የሚያረክሰው ከአፉ የሚወጣው እንጂ ወደ አፉ የሚገባው አይደለም።”
12ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው፣ “ፈሪሳውያን ያልኸውን ሰምተው እንደ ተቈጡ ዐወቅህ?” አሉት።
13እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። 14ተዉአቸው፣ እነርሱ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውር መሪዎች ናቸው፤ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ተያይዘው ገደል ይገባሉ።”
15ጴጥሮስም፣ “ምሳሌውን አስረዳን” አለው።
16እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተም እስካሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን? 17በአፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ ዘልቆ፣ ከዚያም ወደ ውጭ እንደሚወጣ አታውቁምን? 18ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይመነጫል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ይህ ነው፤ 19ክፉ ሐሳብ፣ ነፍስ መግደል፣ ማመንዘር፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በሐሰት መመስከርና ስም ማጕደፍ ከልብ ይመነጫሉና። 20ሰውን የሚያረክሱ እነዚህ ናቸው እንጂ እጅን ሳይታጠቡ መብላት ሰውን አያረክስም።”
የከነዓናዊቷ ሴት እምነት
15፥21-28 ተጓ ምብ – ማር 7፥24-30
21ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። 22አንዲት ከነዓናዊት ሴት ከዚያ አካባቢ በመውጣት ወደ ኢየሱስ መጥታ፣ “ጌታ ሆይ፤ የዳዊት ልጅ፤ ራራልኝ፤ ልጄ በርኩስ መንፈስ ተይዛ በጣም ትሠቃያለች” ብላ ጮኸች።
23እርሱ ግን አንድም ቃል አልመለሰላትም፤ በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “እየተከተለችን ትጮኻለችና ብታሰናብታትስ?” ብለው ጠየቁት።
24እርሱም፣ “የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ሆነው ወደ ጠፉት በጎች ብቻ ነው” አለ።
25ሴትዮዋም እግሩ ላይ ወድቃ፣ “ጌታ ሆይ፤ ርዳኝ” አለች።
26እርሱም መልሶ፣ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መወርወር አይገባም” አላት።
27እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ ውሾችም እኮ ከጌታቸው ማዕድ የወዳደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለችው።
28በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ “አንቺ ሴት እምነትሽ ታላቅ ነው! እንደ ፈለግሽው ይሁንልሽ” አላት። ልጇም ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰች።
ኢየሱስ አራት ሺሕ ሰዎች በታምር መገበ
15፥29-31 ተጓ ምብ – ማር 7፥31-37
15፥32-39 ተጓ ምብ – ማር 8፥1-10
15፥32-39 ተጓ ምብ – ማቴ 14፥13-21
29ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ በገሊላ ባሕር አጠገብ ወዳለው ስፍራ በመሄድ ወደ ተራራ ወጥቶ ተቀመጠ። 30ቍጥሩ ብዙ የሆነ ሕዝብም ዐንካሶችን፣ ዐይነ ስውሮችን፣ ሽባዎችን፣ ዲዳዎችን እንዲሁም ሌሎች ብዙዎችን ሕመምተኞች ይዘው ወደ እርሱ በማምጣት በእግሩ ሥር አስቀመጧቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። 31ሕዝቡም ዲዳው ሲናገር፣ ሽባው ደኅና ሲሆን፣ ዐንካሳው ቀጥ ብሎ ሲሄድ፣ ዐይነ ስውሩም ሲያይ ተመልክተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አመሰገኑ።
32ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፣ “ሕዝቡ ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ስለሆናቸውና የሚበሉት ስለሌላቸው ዐዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድ ላይ በራብ ዝለው እንዳይወድቁ ጦማቸውን ልሰድዳቸው አልፈቅድም” አለ።
33ደቀ መዛሙርቱም፣ “በዚህ ምንም በሌለበት ምድረ በዳ ይህን ሁሉ ሕዝብ ለማብላት በቂ እንጀራ ከየት እናገኛለን?” አሉት።
34ኢየሱስም፣ “ለመሆኑ ስንት እንጀራ አላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
እነርሱም፣ “ሰባት እንጀራና ጥቂት ትንንሽ ዓሣ” አሉት።
35እርሱም ሕዝቡን መሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዛቸው፤ 36ሰባቱን እንጀራና ዓሣውን ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አከፋፈሉ። 37ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱም የተረፈውን ቍርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ። 38የበሉትም ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ አራት ሺሕ ወንዶች ነበሩ። 39ኢየሱስ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ፣ በጀልባ ወደ መጌዶል ሄደ።
Currently Selected:
ማቴዎስ 15: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.