በዚያን ጊዜ የአራተኛው ክፍል ገዥ የነበረው፣ ሄሮድስ ስለ ኢየሱስ ዝና ሰማ፤ ባለሟሎቹንም፣ “እንዲህ ከሆነ መጥምቁ ዮሐንስ ከሞት ተነሥቶ መጥቷል ማለት ነው፤ ይህ ሁሉ ድንቅ ታምራት በእርሱ የሚደረገውም ለዚህ ነው” አላቸው። ቀደም ሲል ሄሮድስ፣ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ ወህኒ አስገብቶት ነበር። ምክንያቱም ዮሐንስ፣ “እርሷን እንድታገባ ሕግ አይፈቅድልህም” ይለው ነበር። ሄሮድስም ዮሐንስን ሊገድለው ፈልጎ፣ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ይመለከተው ስለ ነበር ፈራ። ሄሮድስ የልደቱን ቀን ሲያከብር፣ የሄሮድያዳ ልጅ በዘፈን ደስ ስላሰኘችው፣ የምትጠይቀውን ሁሉ ሊሰጣት በመሐላ ቃል ገባላት። ልጅቷም በእናቷ ተመክራ፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በሳሕን ላይ አድርገህ አሁኑኑ ስጠኝ” አለችው። በዚህ ጊዜ ንጉሡ ዐዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከእርሱ ጋር ስለ ነበሩ እንግዶች ሲል ጥያቄዋ እንዲፈጸምላት አዘዘ። ልኮም በወህኒ ውስጥ እንዳለ የዮሐንስን ራስ አስቈረጠ። የተቈረጠውንም ራስ በሳሕን ላይ አድርገው ለልጂቱ ሰጧት፤ ልጂቱም ወስዳ ለእናቷ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም አስከሬኑን ወስደው ቀበሩት፤ ከዚያም ሄደው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስ የሆነውን ነገር በሰማ ጊዜ፣ ከነበረበት ተነሥቶ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ በጀልባ ሄደ። ሕዝቡም ይህን ሰምተው፣ ከየከተማው በእግር ተከተሉት። ኢየሱስም ከጀልባው ሲወርድ ብዙ ሕዝብ አይቶ ራራላቸው፤ ሕመምተኞቻቸውንም ፈወሰላቸው። እየመሸ በመሄዱም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ይህ ስፍራ ምንም የማይገኝበት ምድረ በዳ ነው፤ ጊዜው እየመሸ ስለሆነ፣ ወደ መንደሮች ሄደው የሚበሉት ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት” አሉት። ኢየሱስ ግን፣ “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ የሚበሉትን እናንተ ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፣ “በዚህ ያለን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ነው” አሉት። እርሱም፣ “እስቲ ያለውን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው። ከዚያም ሕዝቡ በሣሩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ዐይኑን ወደ ሰማይ በማቅናት አመስግኖና ባርኮ እንጀራውን ቈረሰ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሰጠ፤ እነርሱም ለሕዝቡ ሰጡ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ የተረፈውን ቍርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። የበሉትም ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ፣ አምስት ሺሕ ወንዶች ያህሉ ነበር። ወዲያውኑ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ተሳፍረው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት አዘዛቸውና እርሱ ሕዝቡን ለማሰናበት ወደ ኋላ ቀረት አለ። ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላም ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ፤ በጨለመም ጊዜ ብቻውን በዚያው ነበር፤ በዚያ ጊዜ ጀልባዋ ባሕሩን ዘልቃ እየተጓዘች ሳለች ነፋስ ተነሥቶ በማዕበል ትንገላታ ጀመር። ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት መጣ። ደቀ መዛሙርቱም በባሕሩ ላይ እየተራመደ ሲመጣ ባዩት ጊዜ ፈሩ፤ እነርሱም፣ “ምትሀት ነው!” በማለት በፍርሀት ጮኹ። ኢየሱስም ወዲያውኑ፣ “አይዟችሁ፤ እኔ ነኝ አትፍሩ” አላቸው። ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ከሆንህስ፣ በውሃው ላይ እየተራመድሁ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው። እርሱም፣ “ና” አለው። ጴጥሮስም፣ ከጀልባው ወርዶ በውሃው ላይ እየተራመደ ወደ ኢየሱስ አመራ። ነገር ግን የነፋሱን ኀይል ባየ ጊዜ ፈራ፤ መስጠምም ሲጀምር፣ “ጌታ ሆይ፤ አድነኝ!” ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም ወዲያውኑ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፣ “አንተ እምነት የጐደለህ፤ ለምን ተጠራጠርህ?” አለው። ኢየሱስና ጴጥሮስ ጀልባው ላይ እንደ ወጡ ነፋሱ ጸጥ አለ። ከዚያም በጀልባው ውስጥ የነበሩት፣ “በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት። ባሕሩን ከተሻገሩ በኋላ ጌንሴሬጥ ወደ ተባለ ቦታ ደረሱ። ነዋሪዎቹም ኢየሱስ መሆኑን ባወቁ ጊዜ፣ በዙሪያው ወዳለ አካባቢ ሁሉ መልእክት ላኩ፤ የታመሙትን ሁሉ ወደ እርሱ በማስመጣት፣ በሽተኞቹ የልብሱን ጫፍ ብቻ ይነኩ ዘንድ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ የነኩትም ሁሉ ተፈወሱ።
ማቴዎስ 14 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 14
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 14:1-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos