የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሚልክያስ 2:10-16

ሚልክያስ 2:10-16 NASV

ሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለንምን? የፈጠረንስ አንድ አምላክ አይደለምን? ታዲያ እርስ በርሳችን ታማኝነት በማጕደል የአባቶቻችንን ኪዳን ለምን እናረክሳለን? ይሁዳ አልታመነም፤ በእስራኤልና በኢየሩሳሌምም አስጸያፊ ነገር ተፈጽሟል፤ ይሁዳ የባዕድ አምላክ ሴት ልጅ በማግባት እግዚአብሔር የሚወድደውን መቅደስ አርክሷል። ይህን የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ቢሆን፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ቍርባን ቢያመጣም እንኳ፣ እግዚአብሔር ከያዕቆብ ድንኳን ያስወግደው። ሌላው የምታደርጉት ነገር ደግሞ፣ የእግዚአብሔርን መሠዊያ በእንባ ታጥለቀልቃላችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ቍርባናችሁን ስለማይመለከትና በደስታም ከእጃችሁ ስለማይቀበል ታለቅሳላችሁ፤ ትጮኻላችሁም። እናንተም፣ “ለምን ይህ ሆነ?” ብላችሁ ትጠይቃላችሁ። ይህ የሆነው የትዳር ጓደኛህን፣ አጋርህንና የቃል ኪዳን ሚስትህን አታልለሃታልና፣ እግዚአብሔር በአንተና በወጣትነት ሚስትህ መካከል ላለው ቃል ኪዳን ምስክር ስለሆነ ነው። እግዚአብሔር አንድ አላደረጋቸውምን? በሥጋም በመንፈስም የእርሱ ናቸው። ለምን አንድ አደረጋቸው? ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለውን ዘር ይፈልግ ስለ ነበር ነው። ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ከወጣትነት ሚስታችሁም ጋር ያላችሁን ታማኝነት አታጓድሉ። “ፍችን እጠላለሁ” ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፤ “ልብሱን በግፍ ድርጊት የሚሸፍነውንም ሰው እጠላለሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት። ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ታማኝነታችሁም አይጓደል።