የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 9:46-62

ሉቃስ 9:46-62 NASV

ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ በደቀ መዛሙርቱ መካከል ክርክር ተነሣ። ኢየሱስም የልባቸውን ሐሳብ ተረድቶ፣ አንድ ሕፃን ይዞ በአጠገቡ አቆመ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል ማንም ቢኖር እኔን ይቀበላል፤ እኔን የሚቀበል ደግሞ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ከሁሉ ይበልጣልና።” ዮሐንስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየነው፤ ከእኛ ጋራ ሆኖ ስለማይከተል ልንከለክለው ሞከርን” አለው። ኢየሱስም፣ “አትከልክሉት፤ የማይቃወማችሁ ሁሉ እርሱ ከእናንተ ጋራ ነውና” አለው። ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚያርግበት ጊዜ በመቃረቡ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቈርጦ ተነሣ፤ አስቀድሞም መልእክተኞችን ወደዚያ ላከ። እነርሱም ሁኔታዎችን አስቀድመው ሊያመቻቹለት ወደ አንድ የሳምራውያን መንደር ገቡ። ሕዝቡ ግን ወደ ኢየሩሳሌም እያመራ መሆኑን ስላወቁ አልተቀበሉትም። ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ሲያዩ፣ “ጌታ ሆይ፤ ኤልያስ እንዳደረገው ሁሉ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው እንድናዝዝ ትፈቅዳለህን?” አሉት። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና፣ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ። በመንገድ ሲሄዱም አንድ ሰው ቀርቦ፣ “ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው። ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጐጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ዐንገቱን እንኳ የሚያስገባበት የለውም” አለው። ሌላውን ሰው ግን፣ “ተከተለኝ” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አስቀድሜ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ሙታን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው፤ አንተ ግን ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” አለው። ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ መከተልስ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን ልመለስና መጀመሪያ የቤቴን ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለ። ኢየሱስ ግን፣ “ዕርፍ ጨብጦ ወደ ኋላ የሚመለከት ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” አለው።