በማግስቱም ከተራራው ከወረዱ በኋላ፣ ብዙ ሕዝብ መጥቶ ኢየሱስን አገኘው። በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “መምህር ሆይ፤ ያለኝ ልጅ እርሱ ብቻ ስለ ሆነ፣ ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ። መንፈስ ሲይዘው በድንገት ይጮኻል፤ ዐረፋ እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፤ ጕዳትም ካደረሰበት በኋላ በስንት መከራ ይተወዋል፤ ደቀ መዛሙርትህ እንዲያወጡለት ለመንኋቸው፤ ነገር ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም “የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋራ እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው!” አለ። ልጁ በመምጣት ላይ ሳለም ጋኔኑ መሬት ላይ ጥሎ አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኩሱን መንፈስ ገሥጾ ልጁን ፈወሰው፤ ለአባቱም መልሶ ሰጠው። ሰዎቹም ሁሉ በእግዚአብሔር ታላቅነት ተገረሙ። እርሱ ባደረገው ሁሉ ሰዎች ሁሉ እየተገረሙ ሳሉ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ይህን የምነግራችሁን ነገር ልብ በሉ፤ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ዐልፎ ይሰጣልና” አለ። እነርሱ ግን ይህን አባባል አልተረዱም፤ እንዳያስተውሉ ነገሩ ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለዚህ ነገር መልሰው እንዳይጠይቁትም ፈሩ። ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ በደቀ መዛሙርቱ መካከል ክርክር ተነሣ። ኢየሱስም የልባቸውን ሐሳብ ተረድቶ፣ አንድ ሕፃን ይዞ በአጠገቡ አቆመ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል ማንም ቢኖር እኔን ይቀበላል፤ እኔን የሚቀበል ደግሞ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ከሁሉ ይበልጣልና።” ዮሐንስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየነው፤ ከእኛ ጋራ ሆኖ ስለማይከተል ልንከለክለው ሞከርን” አለው። ኢየሱስም፣ “አትከልክሉት፤ የማይቃወማችሁ ሁሉ እርሱ ከእናንተ ጋራ ነውና” አለው። ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚያርግበት ጊዜ በመቃረቡ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቈርጦ ተነሣ፤ አስቀድሞም መልእክተኞችን ወደዚያ ላከ። እነርሱም ሁኔታዎችን አስቀድመው ሊያመቻቹለት ወደ አንድ የሳምራውያን መንደር ገቡ። ሕዝቡ ግን ወደ ኢየሩሳሌም እያመራ መሆኑን ስላወቁ አልተቀበሉትም። ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ሲያዩ፣ “ጌታ ሆይ፤ ኤልያስ እንዳደረገው ሁሉ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው እንድናዝዝ ትፈቅዳለህን?” አሉት። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና፣ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ። በመንገድ ሲሄዱም አንድ ሰው ቀርቦ፣ “ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው። ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጐጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ዐንገቱን እንኳ የሚያስገባበት የለውም” አለው። ሌላውን ሰው ግን፣ “ተከተለኝ” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አስቀድሜ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ሙታን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው፤ አንተ ግን ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” አለው። ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ መከተልስ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን ልመለስና መጀመሪያ የቤቴን ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለ። ኢየሱስ ግን፣ “ዕርፍ ጨብጦ ወደ ኋላ የሚመለከት ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” አለው።
ሉቃስ 9 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 9
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 9:37-62
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos