የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 8:41-56

ሉቃስ 8:41-56 NASV

በዚህ ጊዜ ኢያኢሮስ የተባለ የምኵራብ አለቃ መጥቶ፣ በኢየሱስ እግር ላይ በመውደቅ ወደ ቤቱ እንዲሄድለት ለመነው፤ ይህን ልመና ያቀረበው ዕድሜዋ ዐሥራ ሁለት ዓመት የሆነ አንዲት ልጅ ስለ ነበረችው ነው፤ እርሷ በሞት አፋፍ ላይ ነበረች። ወደዚያው እያመራ ሳለ፣ ሕዝቡ በመጋፋት እጅግ ያጨናንቀው ነበር። ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች አንዲት ሴት ነበረች፤ ያላትን ሁሉ ለባለ መድኀኒቶች ጨርሳ ሊፈውሳትም የቻለ ማንም አልነበረም። እርሷም ከበስተ ኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ነካች፤ ይፈስስ የነበረው ደሟም ወዲያው ቆመ። ኢየሱስም፣ “የነካኝ ማነው?” አለ። ሁሉም መንካታቸውን በካዱ ጊዜ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ ሕዝቡ ሁሉ ከብቦህ በግፊያ እያስጨነቀህ ነው” አለው። ኢየሱስ ግን፣ “አንድ ሰው ነክቶኛል፤ ኀይል ከእኔ እንደ ወጣ ዐውቃለሁና” አለ። ሴትዮዋም ሳትታወቅ መሄድ እንዳልቻለች በተረዳች ጊዜ፣ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ ለምን እንደ ነካችውና እንዴት ወዲያው እንደ ተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት ተናገረች። እርሱም፣ “ልጄ ሆይ እምነትሽ ፈውሶሻል በሰላም ሂጂ” አላት። ኢየሱስ ገና እየተናገረ ሳለ፣ አንድ ሰው ከምኵራብ አለቃው ከኢያኢሮስ ቤት መጥቶ፣ “ልጅህ ሞታለች፤ ከዚህ በኋላ መምህሩን አታድክመው” አለው። ኢየሱስም ይህን ሰምቶ ኢያኢሮስን፣ “አትፍራ፣ እመን ብቻ እንጂ፤ ልጅህ ትድናለች” አለው። ወደ ኢያኢሮስ ቤት ሲገባም ከጴጥሮስ፣ ከዮሐንስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከልጅቱ አባትና እናት በቀር ማንም አብሮት እንዲገባ አልፈቀደም። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ሁሉ እያለቀሱላት ዋይ ዋይ ይሉ ነበር። እርሱ ግን፣ “አታልቅሱ፤ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። ሰዎቹም መሞቷን ስላወቁ ሣቁበት። እርሱ ግን እጇን ይዞ፣ “ልጄ ሆይ፤ ተነሺ” አላት። የልጅቷም መንፈስ ተመለሰ፤ ወዲያውም ተነሥታ ቆመች፤ ኢየሱስም የሚበላ ነገር እንዲሰጧት አዘዛቸው። ወላጆቿም ተደነቁ፤ እርሱ ግን የሆነውን ነገር ለማንም እንዳያወሩ አዘዛቸው።