ከዚህ በኋላ ከገሊላ ባሻገር ወዳለው ወደ ጌርጌሴኖን አገር በጀልባ ተሻገሩ። ኢየሱስ ከጀልባዋ ወደ ምድር በወረደ ጊዜ፣ አጋንንት ያደረበት አንድ ሰው ከከተማ ወጥቶ አገኘው፤ ይህ ሰው ለብዙ ጊዜ ልብስ ሳይለብስ፣ በቤትም ሳይኖር የመቃብርን ስፍራ ቤቱ ያደረገ ነበር። ኢየሱስንም ባየው ጊዜ እየጮኸ ፊቱ ተደፋ፤ በታላቅ ድምፅም፣ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ጋር ምን ጕዳይ አለህ? እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ” አለ። ርኩሱ መንፈስ ይህን ያለው ከሰውየው እንዲወጣ ኢየሱስ አዝዞት ስለ ነበር ነው። ርኩሱ መንፈስ በየጊዜው ስለሚነሣበት ሰውየው በሰንሰለትና በእግር ብረት እየታሰረ ቢጠበቅም፣ የታሰረበትን ሰንሰለት እየበጣጠሰ ያደረበት ጋኔን ወደ በረሓ ይነዳው ነበር። ኢየሱስም፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም ብዙ አጋንንት ገብተውበት ስለ ነበር፣ “ሌጌዎን” አለው። አጋንንቱም እንጦርጦስ ግቡ ብሎ እንዳያዝዛቸው አጥብቀው ለመኑት። በዚያም አካባቢ በተራራ ወገብ ላይ የብዙ ዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ አጋንንቱም ወደ ዐሣማው መንጋ ግቡ ብሎ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ እርሱም ፈቀደላቸው። አጋንንቱም ከሰውየው ወጥተው ወደ ዐሣማዎቹ ገቡ፤ የዐሣማውም መንጋ በገደሉ አፋፍ ቍልቍል በመንደርደር ባሕሩ ውስጥ ገብቶ ሰጠመ። እረኞቹም የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ፣ ሸሽተው በመሄድ በከተማውና በገጠሩ አወሩ። ሕዝቡም የተደረገውን ነገር ለማየት ከያሉበት ወጥተው ወደ ኢየሱስ መጡ። አጋንንት የወጡለትም ሰው ልብስ ለብሶ፣ ወደ ልቦናው ተመልሶ፣ በኢየሱስም እግር ሥር ተቀምጦ ባዩት ጊዜ ፈሩ። በአጋንንት የተያዘው ሰው ሲድን ያዩትም፣ እንዴት እንደ ዳነ ለሕዝቡ አወሩላቸው። የጌርጌሴኖን አካባቢ ሰዎችም ሁሉ ታላቅ ፍርሀት ስላደረባቸው፣ ከዚያ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ለመኑት፤ እርሱም ወደ ጀልባው ገብቶ ተመልሶ ሄደ። አጋንንት የወጡለትም ሰው አብሮት ለመሆን ኢየሱስን ለመነው፤ እርሱ ግን እንዲህ ሲል አሰናበተው፤ “ወደ ቤትህ ተመልሰህ፣ እግዚአብሔር ያደረገልህን ታላቅ ነገር ተናገር።” ሰውየውም ኢየሱስ ያደረገለትን ታላቅ ነገር በከተማው ሁሉ በይፋ እየተናገረ ሄደ። ሕዝቡ ሁሉ መምጣቱን ይጠባበቁ ስለ ነበር፣ ኢየሱስ በተመለሰ ጊዜ በደስታ ተቀበሉት። በዚህ ጊዜ ኢያኢሮስ የተባለ የምኵራብ አለቃ መጥቶ፣ በኢየሱስ እግር ላይ በመውደቅ ወደ ቤቱ እንዲሄድለት ለመነው፤ ይህን ልመና ያቀረበው ዕድሜዋ ዐሥራ ሁለት ዓመት የሆነ አንዲት ልጅ ስለ ነበረችው ነው፤ እርሷ በሞት አፋፍ ላይ ነበረች። ወደዚያው እያመራ ሳለ፣ ሕዝቡ በመጋፋት እጅግ ያጨናንቀው ነበር። ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች አንዲት ሴት ነበረች፤ ያላትን ሁሉ ለባለ መድኀኒቶች ጨርሳ ሊፈውሳትም የቻለ ማንም አልነበረም። እርሷም ከበስተ ኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ነካች፤ ይፈስስ የነበረው ደሟም ወዲያው ቆመ። ኢየሱስም፣ “የነካኝ ማነው?” አለ። ሁሉም መንካታቸውን በካዱ ጊዜ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ ሕዝቡ ሁሉ ከብቦህ በግፊያ እያስጨነቀህ ነው” አለው። ኢየሱስ ግን፣ “አንድ ሰው ነክቶኛል፤ ኀይል ከእኔ እንደ ወጣ ዐውቃለሁና” አለ። ሴትዮዋም ሳትታወቅ መሄድ እንዳልቻለች በተረዳች ጊዜ፣ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ ለምን እንደ ነካችውና እንዴት ወዲያው እንደ ተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት ተናገረች። እርሱም፣ “ልጄ ሆይ እምነትሽ ፈውሶሻል በሰላም ሂጂ” አላት። ኢየሱስ ገና እየተናገረ ሳለ፣ አንድ ሰው ከምኵራብ አለቃው ከኢያኢሮስ ቤት መጥቶ፣ “ልጅህ ሞታለች፤ ከዚህ በኋላ መምህሩን አታድክመው” አለው። ኢየሱስም ይህን ሰምቶ ኢያኢሮስን፣ “አትፍራ፣ እመን ብቻ እንጂ፤ ልጅህ ትድናለች” አለው። ወደ ኢያኢሮስ ቤት ሲገባም ከጴጥሮስ፣ ከዮሐንስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከልጅቱ አባትና እናት በቀር ማንም አብሮት እንዲገባ አልፈቀደም። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ሁሉ እያለቀሱላት ዋይ ዋይ ይሉ ነበር። እርሱ ግን፣ “አታልቅሱ፤ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። ሰዎቹም መሞቷን ስላወቁ ሣቁበት። እርሱ ግን እጇን ይዞ፣ “ልጄ ሆይ፤ ተነሺ” አላት። የልጅቷም መንፈስ ተመለሰ፤ ወዲያውም ተነሥታ ቆመች፤ ኢየሱስም የሚበላ ነገር እንዲሰጧት አዘዛቸው። ወላጆቿም ተደነቁ፤ እርሱ ግን የሆነውን ነገር ለማንም እንዳያወሩ አዘዛቸው።
ሉቃስ 8 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 8
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 8:26-56
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos