ሉቃስ 4:1-32

ሉቃስ 4:1-32 NASV

ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ እንደ ተመለሰ፣ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፤ በዚያም አርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ፤ በእነዚያም ቀናት ምንም ሳይበላ ከቈየ በኋላ በመጨረሻ ተራበ። ዲያብሎስም፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ ይህን ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዘው” አለው። ኢየሱስም፣ “ ‘ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ብሎ መለሰለት። ከዚያም ዲያብሎስ ወደ አንድ ከፍታ ቦታ አውጥቶት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው፤ እንዲህም አለው፤ “የእነዚህ መንግሥታት ሥልጣንና ክብር ሁሉ ለእኔ ተሰጥቷል፤ እኔም ለምወድደው ስለምሰጥ፣ ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ስለዚህ ብትሰግድልኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል።” ኢየሱስም መልሶ፣ “ ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፏል” አለው። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ወስዶ ከቤተ መቅደሱም ዐናት ላይ አውጥቶ፤ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ራስህን ወደ መሬት ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “ ‘ይጠብቁህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል፤ እግርህም ከድንጋይ ጋራ እንዳይጋጭ፣ በእጆቻቸው ያነሡሃል።’ ” ኢየሱስም፣ “ ‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሏል” ብሎ መለሰለት። ዲያብሎስ ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ ትቶት ሄደ። ኢየሱስም በመንፈስ ኀይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ዝናውም በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ወጣ። እርሱም በምኵራባቸው ያስተምር ነበር፤ ሰውም ሁሉ ያመሰግነው ነበር። ከዚያም ወዳደገበት ከተማ ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሊያነብብም ተነሥቶ ቆመ። የነቢዩ ኢሳይያስ ጥቅልል መጽሐፍም ተሰጠው፤ ጥቅልሉንም መጽሐፍ በተረተረው ጊዜ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ክፍል አገኘ፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል።” ከዚያም መጽሐፉን ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መልሶ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብ የነበሩትም ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም፣ “ይህ በጆሯችሁ የሰማችሁት የመጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” ይላቸው ጀመር። ሁሉም ስለ እርሱ በበጎ ይናገሩ ነበር፤ ደግሞም ከአንደበቱ በሚወጣ የጸጋ ቃል እየተገረሙ፣ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር። እርሱም፣ “ ‘ባለመድኀኒት ሆይ፤ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም ስታደርግ የሰማነውን ነገር እዚህ በራስህ ከተማ ደግሞ አድርግ’ የሚለውን ምሳሌ እንደምትጠቅሱብኝ ጥርጥር የለውም” አላቸው። ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ነቢይ በገዛ አገሩ አይከበርም። ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ተዘግቶ ጽኑ ራብ በምድሪቱ ሁሉ ላይ በነበረበት በኤልያስ ዘመን፣ ብዙ መበለቶች በእስራኤል ነበሩ፤ ኤልያስ ከእነዚህ መካከል ወደ አንዷም አልተላከም፤ ነገር ግን በሲዶና አገር በሰራፕታ ወደ ነበረችው መበለት ተላከ። በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነዚያ መካከል ማንም አልነጻም።” በምኵራብ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ በቍጣ ገነፈሉ፤ ከተቀመጡበትም ተነሥተው ከከተማው አስወጡት፤ ቍልቍል ሊጥሉትም ከተማቸው ወደ ተሠራችበት ኰረብታ አፋፍ ወሰዱት፤ እርሱ ግን በመካከላቸው ሰንጥቆ ሄደ። ከዚያም በገሊላ አውራጃ ወደምትገኘው ከተማ ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም በሰንበት ዕለት ሕዝቡን ያስተምር ጀመር፤ የሚናገረው በሥልጣን ስለ ነበር፣ በትምህርቱ ተደነቁ።