ሉቃስ 22:7-30

ሉቃስ 22:7-30 NASV

ከዚህ በኋላ የፋሲካ በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ። ኢየሱስም፣ “የፋሲካን እራት እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ብሎ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው። እነርሱም፣ “የት እንድናሰናዳ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ ወደ ከተማ ስትገቡ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፤ እርሱ ወደሚገባበት ቤት ድረስ ተከተሉት፤ ለቤቱም ባለቤት፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋራ የፋሲካን እራት የምበላበት የእንግዳ ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል’ በሉት። እርሱም በሰገነት ላይ የተሰናዳ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁ።” እነርሱም ሄደው ልክ ኢየሱስ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካንም በዚያ አዘጋጁ። ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋራ በማእድ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፤ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ይህን ፋሲካ አብሬያችሁ ለመብላት በጣም ስመኝ ነበር፤ እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት የዚህ ትርጕም እስኪፈጸም ድረስ ይህን ፋሲካ ዳግመኛ አልበላም።” ጽዋውን ተቀብሎ ካመሰገነ በኋላ እንዲህ አላቸው፤ “ዕንካችሁ፤ ሁላችሁ ከዚህ ተካፈሉ፤ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እስከምትመጣ ድረስ ከወይን ፍሬ አልጠጣም።” እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ፤ ቈርሶም ሰጣቸውና፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፤ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈስሰው ደሜ የሚመሠረት አዲስ ኪዳን ነው። ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ በማእድ ከእኔ ጋራ ናት። የሰው ልጅስ አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ይሄዳል፤ ነገር ግን እርሱን አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት!” እነርሱም ከመካከላቸው ይህን የሚያደርግ ማን ሊሆን እንደሚችል እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር። ደግሞም ከመካከላቸው ማን የሚበልጥ ሆኖ እንደሚቈጠር በእነርሱ ዘንድ ክርክር ተነሣ። እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ ነገሥታት ሕዝቦቻቸውን በኀይል ይገዛሉ፤ በእነርሱ ላይ ሥልጣን ያላቸውም በጎ አድራጊዎች ተብለው ይጠራሉ። በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይሁን፤ ይልቁን ከእናንተ ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ፣ ገዥ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን። ለመሆኑ፣ በማእድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያስተናግድ ማን ይበልጣል? በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አንድ አገልጋይ ነው። እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ፤ ይኸውም በመንግሥቴ ከማእዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ፣ ደግሞም በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እንድትፈርዱ ነው።”