“ኢየሩሳሌም በጦር ሰራዊት ተከብባ በምታዩበት ጊዜ፣ ጥፋቷ መቃረቡን ዕወቁ። በዚያ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በከተማ ያሉትም ከዚያ ይውጡ፤ በገጠር ያሉትም ወደ ከተማዪቱ አይግቡ፤ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይህ የበቀል ጊዜ ነውና። በምድሪቱ ላይ ታላቅ መከራ ይሆናል፤ በዚህም ሕዝብ ላይ ቍጣ ይመጣል፤ ስለዚህ በዚያ ወቅት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ እናቶች ወዮላቸው! በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብም ሁሉ በምርኮ ይወሰዳሉ፤ ኢየሩሳሌምም የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች። “በፀሓይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ላይ ምልክት ይሆናል፤ ከባሕሩና ከሞገድ ድምፅ የተነሣ፣ በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ይጨነቃሉ፤ ይታወካሉም። የሰማያት ኀይላት ስለሚናወጡ፣ ሰዎች በፍርሀትና በዓለም ላይ ምን ይመጣ ይሆን እያሉ በመጠባበቅ ይዝላሉ። በዚያ ጊዜ የሰው ልጅ በኀይልና በታላቅ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። እናንተም እነዚህ ነገሮች መፈጸም ሲጀምሩ፣ መዳናችሁ ስለ ተቃረበ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ወደ ላይ ቀና አድርጉ።” ቀጥሎም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ “በለስንና ዛፎችን ሁሉ ተመልከቱ፤ ቅጠሎቻቸው አቈጥቍጠው ስታዩ፣ በዚያ ጊዜ በጋ መቃረቡን ራሳችሁ ታውቃላችሁ። እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች ዕወቁ። “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም። “እንግዲህ በገደብ የለሽ ሕይወት፣ በመጠጥ ብዛትና ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝልና ያ ቀን እንደ ወጥመድ ድንገት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ ይህ በመላው ምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ ይደርሳልና። ስለዚህ ከሚመጣው ሁሉ እንድታመልጡና በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድትችሉ ሁልጊዜ ተግታችሁ ጸልዩ።” ኢየሱስም ቀን ቀን በቤተ መቅደስ እያስተማረ፣ ሌሊት ግን ደብረ ዘይት ወደ ተባለ ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር። ሕዝቡም ሁሉ ሊሰሙት ማልደው ወደ ቤተ መቅደስ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።
ሉቃስ 21 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 21
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 21:20-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች