ሉቃስ 2:1-24

ሉቃስ 2:1-24 NASV

በዚያ ዘመን፣ የዓለሙ ሁሉ ሕዝብ እንዲቈጠርና እንዲመዘገብ ከአውግስጦስ ቄሳር ትእዛዝ ወጣ። ይህም ቄሬኔዎስ የሶርያ ገዥ በነበረበት ጊዜ የተደረገ የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ ነበር። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ለመመዝገብ ወደየራሱ ከተማ ሄደ። ዮሴፍም ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ፣ በገሊላ አውራጃ ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ የዳዊት ከተማ ወደሆነችው፣ ቤተ ልሔም ወደምትባል ከተማ ወደ ይሁዳ ወጣ። ወደዚያም ለመመዝገብ የተጓዘው፣ የመውለጃ ጊዜዋ ከተቃረበው ከዕጮኛው ከማርያም ጋራ ነበር። በዚያም እንዳሉ የምትወልድበት ጊዜ ደረሰ፤ የበኵር ልጇ የሆነውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ በጨርቅም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማረፊያ ቦታ ስላላገኙ በግርግም አስተኛችው። በዚያው አገር በሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። የጌታም መልአክ ድንገት መጥቶ በአጠገባቸው ቆመ፤ የጌታም ክብር በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅም ፍርሀት ያዛቸው። መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች አምጥቼላችኋለሁና። ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋልና፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው። ይህ ምልክት ይሁናችሁ፤ ሕፃን ልጅ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” ድንገትም ብዙ የሰማይ ሰራዊት ከመልአኩ ጋራ ታዩ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ እንዲህ አሉ፤ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱ ለሚወድዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!” መላእክቱ ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ ከወጡ በኋላ እረኞቹ፣ “ጌታ የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንድናይ ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ” ተባባሉ። እነርሱም ፈጥነው ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን፣ ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። ካዩም በኋላ፣ ስለ ሕፃኑ የተነገራቸውን ገልጠው አወሩ። ይህንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር። እረኞቹም ሁሉም ነገር እንደ ተነገራቸው ሆኖ በማግኘታቸው፣ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ። ስምንት ቀን ሆኖት የመገረዣ ጊዜው ሲደርስ፣ ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስም ኢየሱስ ተባለ። በሙሴ ሕግ መሠረት የመንጻታቸው ወቅት በተፈጸመ ጊዜ፣ ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ለጌታ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ወጡ፤ ይኸውም በጌታ ሕግ፣ “ተባዕት የሆነ በኵር ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል” ተብሎ እንደ ተጻፈ ለመፈጸምና ደግሞም በጌታ ሕግ፣ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፣” መሥዋዕት ለማቅረብ ነበር።